ማቴዎስ 19
19
ስለ መፋታት የቀረበ ጥያቄ
19፥1-9 ተጓ ምብ – ማር 10፥1-12
1ኢየሱስ ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ገሊላን ትቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደ። 2ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ በዚያም ፈወሳቸው።
3ፈሪሳውያንም ሊፈትኑት ቀርበው፣ “አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን እንዲፈታ ተፈቅዷልን?” ሲሉ ጠየቁት።
4እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? 5እንዲህም አለ፤ ‘ስለዚህ፣ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋራ ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ 6ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”
7እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ሙሴ አንድ ወንድ የፍችውን ጽሕፈት ሰጥቶ ሚስቱን እንዲያሰናብት ለምን አዘዘ?” አሉት።
8ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም፤ 9እላችኋለሁ፤ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ፣ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል፤ እርሷንም አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”
10ደቀ መዛሙርቱም፣ “የባልና የሚስት ጕዳይ እንዲህ ከሆነ አለማግባት ይሻላል” አሉት።
11ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ከተሰጣቸው በቀር ይህን ትምህርት ማንም ሊቀበል አይችልም፤ 12ምክንያቱም አንዳንዶች ጃንደረባ ሆነው ይወለዳሉ፤ ሌሎች በሰው እጅ ተሰልበው ጃንደረባ ይሆናሉ፤ ደግሞም ለመንግሥተ ሰማይ ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ የሚያደርጉ አሉ። ይህን መቀበል የሚችል ይቀበል።”
ኢየሱስ ሕፃናትን ባረካቸው
19፥13-15 ተጓ ምብ – ማር 10፥13-16፤ ሉቃ 18፥15-17
13ከዚያም እጆቹን በላያቸው ላይ እንዲጭንባቸውና እንዲጸልይላቸው ሕፃናትን ወደ እርሱ አቀረቧቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ሕፃናቱን ያመጡትን ሰዎች ገሠጿቸው።
14ኢየሱስም፣ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸውም፤ መንግሥተ ሰማይ እንደ እነዚህ ላሉት ናትና” አላቸው። 15እጁንም ከጫነባቸው በኋላ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ሄደ።
የሀብታሙ ጥያቄ
19፥16-29 ተጓ ምብ – ማር 10፥17-30፤ ሉቃ 18፥18-30
16ከዚያም አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ልሥራ” ሲል ጠየቀው።
17ኢየሱስም፣ “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንዱ ብቻ ነው፤ ወደ ሕይወት ለመግባት ከፈለግህ ግን ትእዛዞቹን ጠብቅ” አለው።
18ሰውየውም፣ “የትኞቹን ትእዛዞች?” ሲል ጠየቀ።
ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አትግደል፣ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ 19አባትህንና እናትህን አክብር፤ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።”
20ጕልማሳውም ሰው፣ “እነዚህንማ ጠብቄአለሁ፤ ከዚህ ሌላ የሚጐድለኝ ምን አለ?” አለው።
21ኢየሱስም፣ “ፍጹም ለመሆን ከፈለግህ፣ ሄደህ ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።
22ጕልማሳው ሰውም ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እየተከዘ ሄደ።
23ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ለሀብታም ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት ከባድ ነው። 24ደግሜ እላችኋለሁ፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”
25ይህን ሲሰሙ፣ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ሲሉ ጠየቁ።
26ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው።
27ጴጥሮስም መልሶ፣ “እነሆ፤ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ ምን እናገኝ ይሆን?” አለው።
28ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ በሚመጣው አዲስ ዓለም የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ፣ እናንተም የተከተላችሁኝ በዐሥራ ሁለት ዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ፣ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ ትፈርዳላችሁ። 29ስለ ስሜ ብሎ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን፣#19፥29 አንዳንድ ቅጆች እናትን ወይም ሚስትን ይላሉ። ልጆችን ወይም ዕርሻን የሚተው ሁሉ መቶ ዕጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል። 30ነገር ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች፣ ብዙ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።
Currently Selected:
ማቴዎስ 19: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.