ማቴዎስ 22
22
በሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ
22፥2-14 ተጓ ምብ – ሉቃ 14፥16-24
1ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ የሚል ምሳሌ ነገራቸው፤ 2“መንግሥተ ሰማይ ለልጁ ሰርግ የደገሰን ንጉሥ ትመስላለች፤ 3ንጉሡም የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ ባሮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን አንመጣም አሉ።
4 “እንደ ገናም ሌሎች ባሮች ልኮ፣ ‘የተጋበዙትን፣ እነሆ፣ በሬዎችንና የሠቡ ከብቶቼን ዐርጄ ድግሱን አዘጋጅቻለሁ፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ስለ ሆነ፣ ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው’ አለ።
5 “ተጋባዦቹ ግን ጥሪውን ችላ ብለው፣ አንዱ ወደ ዕርሻው ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ 6የቀሩትም ባሮቹን በመያዝ አጕላልተው ገደሏቸው። 7ንጉሡም በመቈጣት ሰራዊቱን ልኮ ገዳዮቻቸውን አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።
8 “ከዚያም ባሮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘የሰርጉ ድግስ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ፣ 9ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ ጥሩ።’ 10ባሮቹም ወደ ጐዳናዎች ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት።
11 “ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፣ አንድ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፤ 12እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ?’ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም።
13 “ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤
14 “የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”
ግብር ስለ መክፈል
22፥15-22 ተጓ ምብ – ማር 12፥13-17፤ ሉቃ 20፥20-26
15ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ ዕላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። 16ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋራ ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደ ሆንህ፣ ለማንም ሳታደላ ሁሉን እኩል እንደምትመለከት እናውቃለን፤ 17ስለዚህ ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”
18ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? 19ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስኪ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። 20እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው።
21እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” አሉት።
እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።
22ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተዉትም ሄዱ።
ስለ ሙታን ትንሣኤ
22፥23-33 ተጓ ምብ – ማር 12፥18-27፤ ሉቃ 20፥27-40
23በዚያው ቀን፣ ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ ብለው ጠየቁት፤ 24“መምህር ሆይ፤ ሙሴ፣ ‘አንድ ሰው ከሚስቱ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት አግብቶ ለርሱ ዘር ይተካለት’ ብሏል። 25በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ፣ ሚስቱን ወንድሙ አገባት፤ 26እንደዚሁ ደግሞ ሁለተኛውም፣ ሦስተኛውም እስከ ሰባተኛው ድረስ በዚህ ሁኔታ ሞቱ። 27በመጨረሻ ሴትዮዋ ራሷ ሞተች። 28ስለዚህ ሁሉም ስላገቧት በትንሣኤ ቀን ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”
29ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ ትስታላችሁ፤ 30ከትንሣኤ በኋላ ሰዎች እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም። 31ስለ ሙታን ትንሣኤ ግን እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ የተናገራችሁን አላነበባችሁምን? 32‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ።’#22፥32 ዘፀ 3፥6 እግዚአብሔር የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።”
33ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ በትምህርቱ ተደነቁ።
ታላቁ ትእዛዝ
22፥34-40 ተጓ ምብ – ማር 12፥28-31
34ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ሰምተው፣ ፈሪሳውያን በአንድነት ተሰበሰቡ፤ 35ከእነርሱም አንድ የኦሪት ሕግ ዐዋቂ፣ ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ አለው፤ 36“መምህር ሆይ፤ ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትእዛዝ ነው?”
37እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ 38ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ 39ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤#22፥39 ዘሌ 19፥18 40ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዞች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።”
ክርስቶስ የማን ልጅ ነው?
22፥41-46 ተጓ ምብ – ማር 12፥35-37፤ ሉቃ 20፥41-44
41ፈሪሳውያን ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ፣ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ 42“ስለ ክርስቶስ#22፥42 ወይም መሲሑ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው?”
እነርሱም፣ “የዳዊት ልጅ ነው” አሉት።
43እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ታዲያ፣ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ለምን ‘ጌታዬ’ ይለዋል? ለምንስ፣ እንዲህ ይለዋል?
44 “ ‘ጌታ ጌታዬን፤
“ጠላቶችህን ከእግሮችህ በታች
እስከማደርግልህ ድረስ፣
በቀኜ ተቀመጥ።” ’ # 22፥44
መዝ 110፥1
45 ስለዚህ ዳዊት፣ ‘ጌታዬ’ ብሎ ከጠራው፣ እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?” 46አንድ ቃል ሊመልስለት የቻለ ወይም ከዚያ ቀን ጀምሮ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።
Currently Selected:
ማቴዎስ 22: NASV
Highlight
Share
Copy
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fen.png&w=128&q=75)
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.