ማቴዎስ 25
25
የዐሥሩ ልጃገረዶች ምሳሌ
1 “በዚያ ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ልጃገረዶችን ትመስላለች። 2ከእነርሱም ዐምስቱ ልጃገረዶች ዝንጉዎች፣ ዐምስቱ ደግሞ አስተዋዮች ነበሩ፤ 3ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር። 4አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋራ መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር። 5ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።
6 “እኩለ ሌሊት ላይ፣ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ።
7 “በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ። 8ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው።
9 “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው።
10 “ዘይት ሊገዙ እንደ ሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ ዐብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።
11 “ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ።
12 “እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።
13 “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።
የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ
25፥14-30 ተጓ ምብ – ሉቃ 19፥12-27
14 “የእግዚአብሔር መንግሥት ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ 15ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ ዐምስት ታላንት፣#25፥15 ታላንት የአንድ ቀን ሠራተኛ የኻያ ዓመታት ክፍያን የሚያሳይ በሺሕ የሚቈጠር ብር የሚያህል ነው። ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጕዞውን ቀጠለ። 16ዐምስት ታላንት የተቀበለው ሰው፣ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ ዐምስት ታላንት አተረፈ፤ 17እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ 18አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።
19 “የባሪያዎቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። 20ዐምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ ዐምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ዐምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ ዐምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።
21 “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ ባሪያ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
22 “እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።
23 “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ ባሪያ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
24 “አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ 25ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው።
26 “ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ ባሪያ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል? 27ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር።
28 “ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤ 29ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 30ይህን የማይረባ ባሪያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።
የመጨረሻው ፍርድ
31 “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋራ በክብሩ ሲመጣ፣ በክብሩ ዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ 32ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እርሱም፣ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ፣ ሕዝቡን አንዱን ከሌላው ይለያል፤ 33በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያቆማቸዋል።
34 “በዚያ ጊዜ ንጉሡ በቀኙ በኩል ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፤ 35ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ 36ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ አስታምማችሁኛል፤ ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’
37 “ጻድቃንም መልሰው እንዲህ ይሉታል፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይም ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? 38እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? 39እንዲሁም ታምመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’
40 “ንጉሡም መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል።
41 “ከዚያም በግራው በኩል ላሉት ደግሞ እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንተ የተረገማችሁ፤ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው የዘላለም እሳት ከእኔ ተለይታችሁ ሂዱ፤ 42ምክንያቱም ተርቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፤ 43እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’
44 “እነርሱም መልሰው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ ወይም ተጠምተህ፣ እንግዳ ሆነህ ወይም ታርዘህ፣ ታምመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ አልደረስንልህም’ ይሉታል።
45 “በዚያ ጊዜ እርሱም መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ አለማድረጋችሁ፣ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል።
46 “እነዚህም ወደ ዘላለም ፍርድ፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”
Currently Selected:
ማቴዎስ 25: NASV
Highlight
Share
Copy
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fen.png&w=128&q=75)
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.