YouVersion Logo
Search Icon

የያዕቆብ መልእክት 3

3
ምላስን ስለ መቈጣጠር
1ወንድሞቼ ሆይ! እኛ አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁና ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ። 2እኛ ሁላችን ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን፤ በንግግሩ የማይሳሳት እርሱ ሰውነቱን መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው። 3ፈረስ እንዲታዘዝልን በአፉ ውስጥ ልጓም እናገባለን፤ ፈረሱንም ወደምንፈልገው ቦታ እንመራዋለን። 4መርከብ ምንም ትልቅ ቢሆንና በኀይለኛ ነፋስ የሚገፋ ቢሆንም፥ የመርከቡ ነጂ በትንሽ መቅዘፊያ ወደ ፈለገው ቦታ ይነዳዋል። 5እንዲሁም ምላስ ትንሽ የአካል ክፍል ስትሆን በታላላቅ ነገሮች ትመካለች፤ ትልቅ ጫካ የሚቃጠለው በትንሽ እሳት ነው። 6ምላስም እንደ እሳት ናት፤ ምላስ በአካል ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ ክፉ ዓለም ናት፤ አካላችንን ትበክላለች፤ ከገሃነም እንደሚወጣ እሳትም የኑሮአችንን ሂደት ሁሉ ታቃጥላለች። 7የምድር አውሬዎችና ወፎች፥ በመሬት የሚሳቡና በባሕር የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሁሉ በሰው ሊገሩ ይችላሉ፤ ደግሞም ተገርተዋል። 8ነገር ግን ምላስን ሊገራ የሚችል ማንም የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት። 9በእርስዋ አባታችንን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፤ እንዲሁም በእርስዋ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። #ዘፍ. 1፥26። 10ከአንድ አፍ ምስጋናና ርግማን ይወጣሉ፤ ወንድሞቼ ሆይ! ይህ ሊሆን አይገባም። 11ከአንድ ምንጭ ለመጠጥ የሚሆን ጣፋጭ ውሃና መራራ ውሃ ሊፈልቅ ይችላልን? 12ወንድሞቼ ሆይ፥ የበለስ ዛፍ የወይራን ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? ወይስ የወይን ተክል የበለስ ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም ከመራራ ውሃ ጣፋጭ ውሃ ሊገኝ ይችላልን?
ሰማያዊና ምድራዊ ጥበብ
13ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ማን ነው? በጥበብና በትሕትና የፈጸመውን ሥራ በመልካም አኗኗሩ ያሳይ። 14ነገር ግን መራራ ቅናትና ራስ ወዳድነት በልባችሁ ቢኖር አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ። 15እንዲህ ዐይነቱ ጥበብ የሚገኘው ከዓለም፥ ከሥጋ፥ ከሰይጣን ነው እንጂ ከእግዚአብሔር አይደለም። 16ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይኖራሉ። 17ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሚገኘው ጥበብ በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ቀጥሎም ሰላም ወዳድ፥ ደግ፥ ታዛዥ፥ ምሕረት አድራጊ፥ ጥሩ ፍሬ የሞላበት፥ አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው። 18ሰላም ወዳድ ሰዎች ሰላምን ዘርተው የጽድቅን ፍሬ ይሰበስባሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in