መጽሐፈ ምሳሌ 11
11
1እግዚአብሔር በሐሰተኛ ሚዛን የሚያታልሉትን ሰዎች ይጠላል፤
በትክክለኛ ሚዛን በሚመዝኑት ሰዎች ግን ይደሰታል።
2ትዕቢት ውርደትን ያስከትላል፤
ትሕትና ግን ጥበብን ያስገኛል።
3ቀጥተኞች ሰዎች ቅንነታቸው ይመራቸዋል።
እምነት የማይጣልባቸው ሰዎች ግን ጠማማነታቸው ያጠፋቸዋል።
4ለመሞት በምትቃረብበት ቀን ሀብትህ አይጠቅምህም፤
ደግነት ግን የሕይወት ዋስትና ይሆንልሃል።
5ደግነት የመልካሙን ሰው ኑሮ ያቃናለታል፤
ክፉ ሰው ግን በገዛ ክፋቱ ይወድቃል።
6ቅን ሰው በደግነቱ ይድናል፤
እምነት የማይጣልበት ሰው ግን የራሱ ክፉ ምኞት ወጥመድ ሆኖ ይይዘዋል።
7ክፉ ሰው ሲሞት ተስፋውም አብሮት ይሞታል፤
በኀይሉ መመካቱም አብሮት ይጠፋል።
8ጻድቅ ከመከራ ይድናል።
መከራው ግን በክፉ ሰው ላይ ይደርሳል።
9እግዚአብሔርን የማያመልኩ በንግግራቸው ሰውን ያጠፋሉ፤
ጻድቃን ግን በዕውቀት ይድናሉ።
10ለጻድቃን፥ ሁሉ ነገር ሲሳካላቸው በከተማው ውስጥ ደስታ ይሆናል።
ክፉዎች ሲጠፉ ደግሞ እልልታ ይሆናል።
11በእውነተኞች ሰዎች በረከት ምክንያት ከተማ እያደገች ትሄዳለች፤
የክፉ ሰዎች መጥፎ ንግግር ግን ወደ ውድቀት ያደርሳታል።
12በንቀት ተናግሮ ሰውን የሚያዋርድ፥
ማስተዋል የጐደለው ነው፤
አስተዋይ ሰው ግን ዝም ይላል።
13ሐሜተኛ ሰው ምሥጢር አይጠብቅም፤
ታማኝ ሰው ግን ምሥጢርን ሰውሮ ይይዛል።
14አማካሪ የሌለው መንግሥት ይወድቃል፤
ብዙ አማካሪዎች ሲኖሩ ግን ዋስትና ይገኛል።
15የማታውቀውን ሰው ዕዳ ለመክፈል ዋስ ብትሆን፥
በችግር ላይ ትወድቃለህ፤
ዋስ መሆን ቢቀርብህ ግን የተሻለ ነው።
16ሞገስ ያላት ሴት ትከበራለች፤
መልካም ጠባይ የሌላት ሴት ግን ውርደት ያገኛታል።
ሰነፍ ሰው ሀብት ማግኘት አይችልም፤
ታታሪ ሰው ግን ሀብታም ይሆናል።
17ርኅሩኅ ብትሆን ራስህን ትጠቅማለህ፤
ጨካኝ ብትሆን ግን ራስህን ትጐዳለህ።
18ክፉ ሰዎች የሚያገኙት ጥቅም አይኖርም፤
ትክክል የሆነውን ነገር ብታደርግ፥
የመልካም ሥራህን ዋጋ ታገኛለህ።
19መልካም ሥራ ለመሥራት ቊርጥ ውሳኔ ያደረገ ሰው በሕይወት ይኖራል፤
ስሕተት በማድረግ የሚጸና ግን ይሞታል።
20እግዚአብሔር ልበ ጠማሞችን ይጸየፋል።
ነቀፋ በሌለበት መንገድ በሚሄዱ ሰዎች ይደሰታል።
21በእርግጥ ክፉ ሰዎች መቀጣታቸው የማይቀር ነው፤
ደጎች ግን ይድናሉ።
22ማስተዋል የጐደላት ቈንጆ ሴት፥
ውበትዋ በዐሣማ አፍንጫ ላይ እንደሚገኝ የወርቅ ጒትቻ ነው።
23የደጋግ ሰዎች ምኞት ጥሩ ውጤት አለው፤
የክፉ ሰዎች ምኞት ግን ጥፋትን ያስከትላል።
24አንዳንድ ሰዎች በለጋሥነት ገንዘባቸውን ይበትናሉ፤
ነገር ግን ሀብታቸው እየበዛ ይሄዳል፤
ሌሎች ደግሞ ያለ ልክ ለገንዘባቸው ይሳሳሉ፤
ነገር ግን ድኽነታቸው እየበዛ ይሄዳል።
25ለጋስ ሁን፤ ትበለጽጋለህ፤
ሌሎችን እርዳ፤ አንተም ርዳታ ታገኛለህ።
26አቈይቶ በውድ ዋጋ ለመሸጥ እህሉን የሚያከማች ሰው፥
በሕዝብ ዘንድ የተረገመ ይሆናል፤
እህሉን ለገበያ የሚያቀርብ ሰው ግን፥
በሕዝብ ዘንድ የተመሰገነ ይሆናል።
27መልካምን ነገር ተግቶ የሚሻ መልካም ነገርን ያገኛል፤
ክፉ ነገርን የሚሠራ ግን ክፉ ነገር ይደርስበታል።
28በሀብታቸው የሚተማመኑ ሰዎች እንደ ቅጠል ይረግፋሉ፤
እውነተኞች ሰዎች ግን እንደ መልካም ተክል ይለመልማሉ።
29በቤተ ሰቡ ላይ ሁከት የሚያመጣ ሰው
ምንም የሚያተርፈው ጥቅም የለም፤
ሞኞች ዘወትር ለጠቢባን አገልጋዮች ይሆናሉ።
30የጻድቅ ሰው ሥራ የዘለዓለም ሕይወትን ያስገኛል፤
ዐመፅ ግን ለሕይወት መጥፋት ምክንያት ይሆናል።
31ደጋግ ሰዎች በምድር ላይ ሳሉ የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ፤
ክፉዎችና ኃጢአተኞች ግን እጅግ የበረታ ቅጣትን ይቀበላሉ። #1ጴጥ. 4፥18።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 11: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997