YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 50

50
1 # ባሮክ 4፥6። ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናታችሁን የፈታሁበት የፍቺዋ ጽሕፈት የት አለ? ወይስ እናንተን የሸጥሁ ከአበዳሪዎች ለየትኛው ነው? እነሆ፥ ስለ ኃጢአታችሁ ተሸጣችኋል፥ ስለ በደላችሁም እናታችሁ ተፈታለች። 2በመጣሁስ ጊዜ ሰው ስለምን አልነበረም? በጠራሁስ ጊዜ የሚመልስ ስለምን አልነበረም? መታደግ እንዳትችል እጄ አጭር ሆናለችን? ወይስ ለማዳን ኃይል የለኝም? እነሆ፥ በገሠጽሁ ጊዜ ባሕርን አደርቃለሁ፥ ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋቸዋለሁ፤ ውኃም አጥተው ዓሦቻቸው ይገማሉ፥ በጥማትም ይሞታሉ። 3ሰማያትን ጥቁረት አለብሳቸዋለሁ፥ መጋረጃቸውንም ማቅ አደርጋለሁ። 4የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ እንዳውቅ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል፤ ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፥ እንደ ተማሪዎችም እንድትሰማ ጆሮዬን ያነቃቃል። 5ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል፥ እኔም ዓመፀኛ አልነበርሁም ወደ ኋላዬም አልተመለስሁም። 6#ማቴ. 26፥67፤ ማር. 14፥65።ጀርባዬን ለገራፊዎች፥ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ፤ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም። 7ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛልና አልታወክሁም፤ ስለዚህም ፊቴን እንደ ባልጩት ድንጋይ አድርጌዋለሁ፥ ኀፍረት ላይ እንደማልወድቅም አውቃለሁ። 8#ሮሜ 8፥33-34።የሚያጸድቀኝ ቅርብ ነው፤ ከእኔስ ጋር የሚከራከር ማን ነው? በአንድነት እንቁም፤ የሚከራከረኝ ማን ነው? ወደ እኔ ይቅረብ። 9እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛል፤ ማን ይፈርድብኛል? እነሆ፥ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃሉ ብልም ይበላቸዋል። 10ከእናንተ ጌታን የሚፈራ፥ የአገልጋዩንም ቃል የሚሰማ፥ በጨለማም የሚሄድ፥ ብርሃንም የሌለው፥ ነገር ግን በጌታ ስም የሚታመን፥ በአምላኩም የሚደገፍ ማን ነው? 11እነሆ፥ እሳት የምታነድዱ፥ የእሳትንም ወላፈን የምትታጠቁ ሁላችሁ፥ በእሳታችሁ ነበልባል ባነደዳችሁትም ወላፈን ሂዱ! ይህ ከእጄ ይሆንባችኋል፤ በኅዘን ትተኛላችሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ትንቢተ ኢሳይያስ 50