ትንቢተ ኢሳይያስ 51
51
1እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ ጌታንም የምትሹ፥ ስሙኝ፤ ከእርሱ የተቈረጣችሁበትን ዐለት ከእርሱም የተቈፈራችሁበትን ጉድጓድ ተመልከቱ። 2ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፥ ባረክሁትም አበዛሁትም። 3ጌታም ጽዮንን ያጽናናል፤ በእርሷም ባድማ የሆነውን ሁሉ ያጽናናል፤ ምድረ በዳዋንም እንደ ዔድን በረሀዋንም እንደ ጌታ ገነት ያደርጋል፤ ደስታና ተድላ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ ይገኝበታል። 4ወገኔ ሆይ፥ አድምጠኝ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ ስማኝ፤ ሕግ ከእኔ ይወጣልና ፍርዴም ለአሕዛብ ብርሃን ይሆናልና። 5ጽድቄ ፈጥኖ ቀርቦአል፥ ማዳኔም ወጥቶአል፥ ክንዴም በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ደሴቶች እኔን በመተማመን ይጠባበቃሉ፥ በክንዴም ይታመናሉ። 6ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንሡ፥ ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያትን እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፥ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፥ የሚኖሩባትም እንዲሁ ይሞታሉ፤ ማዳኔ ግን ለዘለዓለም ይሆናል፥ ጽድቄም አይፈርስም። 7ጽድቅን የምታውቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፥ ስሙኝ፤ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፥ በስድባቸውም አትደንግጡ። 8እንደ ልብስም ብል ይበላቸዋል፥ እንደ በግ ጠጉርም ትል ይበላቸዋል፤ ጽድቄ ግን ለዘለዓለም ማዳኔም ለትውልድ ሁሉ ይሆናል። 9የጌታ ክንድ ሆይ! ተነሥ፥ ተነሥ፥ ኃይልንም ልበስ፤ በቀድሞው ወራትና በጥንቱ ዘመን በነበረው ትውልድ እንደ ሆነው ተነሥ። ረዓብን የቈራረጥህ ዘንዶውንም የወጋህ አንተ አይደለህምን? 10ባሕሩንና የታላቁን ጥልቅ ውኃ ያደረቅከው፥ የዳኑትም እንዲሻገሩ ጥልቁን ባሕር መንገድ ያደረግህ አንተ አይደለህምን? 11ጌታ የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ፤ የዘለዓለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ልቅሶም ይሸሻል። 12የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፥ እኔ ነኝ፤ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ስለምን ትፈራለህ? 13ሰማያትን የዘረጋውን ምድርንም የመሠረተውን ፈጣሪህን ጌታን ረስተሃል፤ ያጠፋ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ ከአስጨናቂው ቁጣ የተነሣ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሃል፤ የአስጨናቂው ቁጣ የት አለ? ምርኮኛው ፈጥኖ ይፈታል፤ 14አይሞትም ወደ ጉድጓድም አይወርድም፥ እንጀራም አይጐድልበትም። 15ሞገዱም እንዲተምም ባሕርን የማናውጥ አምላክህ ጌታ እኔ ነኝ፥ ስሜም የሠራዊት ጌታ ነው። 16ሰማያትን እንድዘረጋ ምድርንም እንድመሠርት፥ ጽዮንንም፦ “አንቺ ሕዝቤ ነሽ” እንድል ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፥ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ። 17#ራእ. 14፥10፤ 16፥19።ከጌታ እጅ የቁጣውን ጽዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ንቂ፥ ንቂ! ቁሚ፤ የሚያንገደግድን ዋንጫ ጠጥተሻል ጨልጠሽውማል። 18ከወለደቻቸው ልጆች ሁሉ የሚመራት የለም፥ ካሳደገቻቸውም ልጆች ሁሉ እጅዋን የሚይዝ የለም። 19እነዚህ ሁለት ነገሮች ሆነውብሻል፥ ማንስ ያስተዛዝንሻል? መፈታትና ጥፋት፥ ራብና ሰይፍ ናቸው፤ እንዴትስ አድርጌ አጽናናሻለሁ? 20ልጆችሽ ዝለዋል፤ በወጥመድ እንደ ተያዘ ሚዳቋ በየአደባባዩ ራስ ላይ ተኝተዋል፤ በጌታ ቁጣና በአምላክሽ ተግሣጽ ተሞልተዋል። 21ስለዚህ ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ ችግረኛ፥ ይህን ስሚ፤ 22ስለ ወገኑ የሚምዋገት አምላክሽ ጌታሽ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የሚያንገደግድን ጽዋ የቁጣዬንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። 23ነፍስሽንም፦ “በአንቺ ላይ እንድንረማመድ ዝቅ በዪ” በሚሉአት በአስጨናቂዎችሽ እጅ አኖረዋለሁ፤ ጀርባሽንም ለሚሻገሩት እንደ መሬትና እንደ መንገድ አደረግሽላቸው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 51: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in