መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 7
7
1የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አወጡ፤ በኮረብታውም ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት አገቡአት፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት እንዲጠብቅ ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት። 2ታቦቲቱም በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠችበት ቀን ጀምሮ ወራቱ ረዘመ፤ ሃያ ዓመትም ሆነ፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ።
ሳሙኤል የእስራኤል መሪ ስለመሆኑ
3ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፥ “በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና ምስሎቻቸውን ከመካከላችሁ አርቁ፤ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድናችኋል” ብሎ ተናገራቸው። 4የእስራኤልም ልጆች የበዓሊምን አማልክትና የአስጣሮትን ምስሎች አራቁ፤ እግዚአብሔርንም ብቻ አመለኩ።
5ሳሙኤልም፥ “እስራኤልን ሁሉ ወደ መሴፋ#ዕብ. “ምጽጳ” ይላል። ሰብስቡ፤ ስለ እናንተም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ” አለ። 6እነርሱም ወደ መሴፋ ተሰበሰቡ፤ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት በምድር ላይ አፈሰሱ፤ በዚያም ቀን ጾሙ፤ በዚያም፥ “በእግዚአብሔር ፊት በድለናል” አሉ። ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በመሴፋ ፈረደ። 7ፍልስጥኤማውያንም የእስራኤል ልጆች ወደ መሴፋ እንደ ተሰበሰቡ በሰሙ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን አለቆች በእስራኤል ላይ ዘመቱ፤ የእስራኤልም ልጆች ሰምተው ከፍልስጥኤማውያን ፊት ፈሩ። 8የእስራኤልም ልጆች ሳሙኤልን፥ “ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ከመጮኽ ዝም አትበል። እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነናል” አሉት። 9ሳሙኤልም አንድ የበግ ጠቦት ወስዶ ለእግዚአብሔር ፈጽሞ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ከሕዝቡ ጋር አቀረበው፤ ሳሙኤልም ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው። 10ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሣርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ የነጐድጓድ ድምፅ አንጐደጐደ፤ ደነገጡም፤ በእስራኤልም ፊት ድል ተመቱ። 11የእስራኤልም ሰዎች ከመሴፋ ወጡ፤ ፍልስጥኤማውያንንም አሳደዱ፤ በቤኮር ታችም እስኪደርሱ ድረስ መቱአቸው።
12ሳሙኤልም አንድ ድንጋይ ወስዶ በመሴፋና በአሮጌው ከተማ መካከል#ዕብ. “በምጽጳና በሼን መካከል” ይላል። አኖረው፤ ስሙንም፥ “እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል” ሲል “አቤንኤዜር” ብሎ ጠራው። እብነ ረድኤት ማለት ነው። 13እግዚአብሔርም ፍልስጥኤማውያንን አዋረዳቸው፤ ዳግመኛም ከዚያ ወዲያ ወደ እስራኤል ድንበር አልወጡም፤ በሳሙኤልም ዘመን ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ነበረች። 14ፍልስጥኤማውያንም ከአስቀሎና ጀምሮ እስከ፤ ጌት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አዞብ” ይላል። ድረስ ከእስራኤል ልጆች የወሰዱአቸው ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱ፤ እስራኤልም ድንበሩን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ወሰዱ። በእስራኤልና በአሞራውያን መካከልም ሰላም ሆነ።
15ሳሙኤልም በዘመኑ ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 16በየዓመቱም ወደ ቤቴል፥ ወደ ጌልጌላና ወደ መሴፋ ይዞር ነበር፤ በእነዚያም በተቀደሱ ስፍራዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 17ቤቱም በዚያ ነበረና ወደ አርማቴም ይመለስ ነበር፤ በዚያም በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 7: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in