ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 12
12
ጳውሎስ ስላየው ራእይ
1እነሆ መመካት ይቻለኛል፤ ነገር ግን አይጠቅምም፤ ደግሞም ወደ ጌታ ራእይና መገለጥ እሄዳለሁ። 2በክርስቶስ ያመነ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ ዘመኑ ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት ነው፤ ነገር ግን በሥጋው ይሁን በነፍሱ እንጃ፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ያን ሰው እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ነጥቀው ወሰዱት። 3ያን ሰው አውቀዋለሁ፤ በሥጋው ይሁን በነፍሱ እንጃ እግዚአብሔር ያውቃል። 4ወደ ገነትም ነጥቀው ወሰዱት፤ በዚያም ሰው ሊናገረው የማይችለውን የማይተረጐም ነገር ሰማ። 5ስለዚህም እንደዚህ ባለው እመካለሁ፤ በመከራዬ እንጂ በራሴስ አልመካም። 6ልመካ ብሻም አላዋቂ አይደለሁም፤ እውነቱን እናገራለሁና፤ ነገር ግን ስላዩኝና ስለ ሰሙኝ እንደምበልጥ አድርገው እንዳይጠራጠሩኝ ትቸዋለሁ። 7ስለዚህም ቢሆን በብዙ ራእይ እንዳልታበይ ሰውነቴን የሚወጋ እርሱም የሚጐስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ። 8ስለዚህም ከእኔ ያርቀው ዘንድ ጌታዬን ሦስት ጊዜ ማለድሁት። 9እርሱም፥ “ጸጋዬ ይበቃሀል፤ ኀይልስ በደዌ ያልቃል” አለኝ፤ የክርስቶስም ኀይል በእኔ ላይ ያድር ዘንድ በመከራዬ ልመካ ወደድሁ። 10ስለዚህም ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበልን፥ መሰደብን፥ መጨነቅን፥ መሰደድን፥ መቸገርንም ወደድሁ፤ መከራ በተቀበልሁ ጊዜ ወዲያውኑ እበረታለሁና።
በቆሮንቶስ ሰዎች ላይ ስለ አደረገው ወቀሳ
11እነሆ እናንተ ስላገበራችሁኝ በመመካቴ ሰነፍ ሆንሁ፤ ለእኔማ በእናንተ ዘንድ ልከብርና እናንተም ምስክሮች ልትሆኑኝ#“እናንተም ምስክሮች ልትሆኑኝ” የሚለው በግሪኩ የለም። ይገባኝ ነበር፤ እኔ እንደ ኢምንት ብሆንም ዋናዎቹ ሐዋርያት ሁሉ ከሠሩት ሥራ ያጐደልሁባችሁ#ግሪኩ “ከዋናዎቹ ሐዋርያት በምንም አልጐድልም” ይላል። የለምና። 12የሐዋርያት ምልክትስ በፍጹም ትዕግሥትና በተአምራት፥ ድንቅ ሥራ በመሥራትና በኀይላት ተደርጎላችኋል። 13እከብድባችሁ ዘንድ ወደ እናንተ ካለመምጣቴ በቀር፥ ከአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ያሳነስኋችሁ በምንድን ነው? ይህቺን በደሌን ይቅር በሉኝ።
14እነሆ ወደ እናንተ ልመጣ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ነገር ግን አልተፋጠንሁም#ግሪኩ “አልከበድሁባችሁም” ይላል። ገንዘባችሁን ያይደለ፥ እናንተን እሻለሁና፤ ልጆች ለወላጆቻቸው ያይደለ ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያከማቹ ይገባልና፤ 15እኔ ግን እጥፍ ድርብ አወጣለሁ፤ ስለ ሕይወታችሁም ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እናንተንም እጅግ ብወዳችሁ ራሴን ወደድሁ። 16እኔ አልከበድሁባችሁም፤ ነገር ግን ምክር ዐዋቂ ሆኜ በመጠበብ ወሰድኋችሁ። 17በውኑ ይህን አድርጉልኝ ብዬ ወደ እናንተ የላክሁት መልእክት አለን? ወይስ የቀማኋችሁ ነገር አለን? እንጃ። 18እነሆ ቲቶን ማለድሁት፤ ከእርሱም ጋር ሌላውን ወንድማችንን ላክሁት፤ በውኑ ቲቶ የበደላችሁ በደል አለን? በእርሱ በአደረው መንፈስ የምንመላለስ፥ እርሱም የሄደበትን ፍለጋ የምንከተል አይደለንምን?
19እኛስ ደግሞ ስለ ራሳችን የምንከራከራችሁ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ይህ ሁሉ ግን እናንተ ትታነጹ ዘንድ ነው። 20ነገር ግን ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ እንደምወደው ሆናችሁ ያላገኘኋችሁ እንደ ሆነ፤ እኔም እንደማትወዱት እሆንባችኋለሁ ብዬ እፈራለሁ፤ ወይም እኮ በመካከላችሁ ክርክር፥ ኵራት፥ መቀናናት፥ መበሳጨት፥ መዘባበት፥ ወይም መተማማት፥ መታወክ፥ ወይም ልብን ማስታበይ ይኖር ይሆናል። 21ወይም እንደ ገና ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔር ያሳዝነኝ ይሆናል፤ በድለው ንስሓ ላልገቡም ስለ ርኵስነታቸውና ስለ መዳራታቸው፥ ስለሚሠሩት ዝሙታቸውም ለብዙዎች አዝን ይሆናል።
Currently Selected:
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 12: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in