ኦሪት ዘዳግም 6
6
ታላቁ ትእዛዝ
1“ልትወርሱአት በምትገቡባት ምድር ታደርጉት ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንዳስተምራችሁ ያዘዘው ትእዛዝና ሥርዐት፥ ፍርድም ይህ ነው። 2እናንተ፥ ልጆቻችሁም፥ የልጅ ልጆቻችሁም በዕድሜአችሁ ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፈርታችሁ እኔ ለእናንተ ያዘዝሁትን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ ትጠብቁ ዘንድ፥ ዕድሜአችሁም ይረዝም ዘንድ፤ 3እስራኤል ሆይ፥ ስማ፦ ማርና ወተት የምታፈስሰውን ምድር ይሰጥህ ዘንድ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ እጅግ እንድትበዛ፥ መልካምም እንዲሆንልህ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ።” ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ያዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ ሁሉ ይህ ነው።#“ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ያዘዛቸው ትእዛዝ ሁሉ ይህ ነው” የሚለው በዕብ. የለም።
4“እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ 5አምላክህንም እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ፥ በፍጹምም ኀይልህ ውደድ። 6እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ፥ በነፍስህም#“በነፍስህም” የሚለው በዕብ. የለም። ያዝ። 7ለልጆችህም አስተምረው፤ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም አስተምረው። 8በእጅህም እንደ ምልክት አድርገው፤ በዐይኖችህም መካከል እንደማይንቀሳቀስ ይሁንልህ። 9በቤትህም መቃኖች፥ በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።
ስለ አለመታዘዝ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
10“አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ባገባህ ጊዜ፤ ያልሠራሃቸውንም ታላቅና መልካም ከተሞች፥ 11ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የሞሉ ቤቶች፥ ያልማስሃቸውንም የተማሱ ጕድጓዶች፥ ያልተከልሃቸውንም ወይንና ወይራ በሰጠህ ጊዜ፥ በበላህና በጠገብህም ጊዜ፤ 12ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። 13አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤ እርሱንም ተከተል#“እርሱንም ተከተል” የሚለው በዕብ. የለም። በስሙም ማል። 14በዙሪያችሁ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎች አማልክት አትከተሉ። 15በመካከልህ ያለው#“በመካከልህ ያለው” የሚለው በግእዝ የለም። አምላክህ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና የአምላክህ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳይነድድብህ፥ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ ተጠንቀቅ።
16“በፈተና ቀን እንደ ፈተንኸው አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው። 17ለአንተ ያዘዘውን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ፥ ምስክሩንም፥ ሥርዐቱንም አጥብቀህ ጠብቅ። 18መልካምም ይሆንልህ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርስዋን ትወርስ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቅኑንና መልካሙን አድርግ። 19እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ያሳድድልህ ዘንድ።
20“ነገ ልጅህ፦ አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዛችሁ ምስክርና ሥርዐት፥ ፍርድስ ምንድን ነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ፥ 21አንተ ልጅህን በለው፦ በግብፅ የፈርዖን ባሪያዎች ነበርን፤ እግዚአብሔርም በጽኑ እጅ፥ በተዘረጋችም ክንድ ከዚያ አወጣን፤ 22እግዚአብሔርም በግብፅና በፈርዖን#ግእዙ “ወመገብቱ ወአግብርቲሁ” የሚል ይጨምራል። በቤቱም ሁሉ ላይ በፊታችን ታላቅና ክፉ ምልክት፥ ተአምራትም አደረገ። 23ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር ያገባንና እርስዋን ይሰጠን ዘንድ እኛን ከዚያ አወጣን። 24እንደ ዛሬም በሕይወት እንዲያኖረን፥ ሁልጊዜም መልካም እንዲሆንልን፥ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፈራ ዘንድ፥ ይህችንም ሥርዐት ሁሉ እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘን። 25እግዚአብሔርም እንዳዘዘን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እናደርጋት ዘንድ ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብንጠብቅ ለእኛ ምሕረት ይሆንልናል።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 6: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in