መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 3
3
እስራኤል የዮርዳኖስን ወንዝ እንደ ተሻገሩ
1ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፤ እርሱና እስራኤልም ሁሉ#“እስራኤልም ሁሉ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ከሰጢም ተጕዘው ወደ ዮርዳኖስ መጡ፤ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ። 2ከሦስት ቀንም በኋላ ጸሓፊዎች በሰፈሩ መካከል ገቡ። 3ለሕዝቡም እንዲህ ብለው ዐወጁ፥ “የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ሌዋውያንና ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት። 4በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን፤ በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ።”
5ኢያሱም ሕዝቡን፥ “ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ራሳችሁን አንጹ” አለ። 6ኢያሱም ካህናቱን፥ “የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት ሂዱ” ብሎ ተናገራቸው፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት ሄዱ።
7እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ በዚህ ቀን በእስራኤል ልጆች ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደርግህ ዘንድ እጀምራለሁ። 8አሁንም አንተ የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት በዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ በዮርዳኖስ ውስጥ ቁሙ ብለህ እዘዝ” አለው።
9ኢያሱም ለእስራኤል ልጆች፥ “ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ” አለ። 10ኢያሱም አለ፥ “ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደ ሆነ፥ እርሱም ከፊታችሁ ከነዓናዊውን፥ ኬጤዎናዊውንም፥ ኤዌዎናዊውንም፥ ፌርዜዎናዊውንም፥ ጌርጌሴዎናዊውንም፥ አሞሬዎናዊውንም፥ ኢያቡሴዎናዊውንም ፈጽሞ እንዲያጠፋቸው በዚህ ታውቃላችሁ። 11እነሆ፥ የምድር ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በፊታችሁ ዮርዳኖስን ትሻገራለች። 12አሁንም ከእስራኤል ነገዶች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ምረጡ፤ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ይሁን። 13እንዲህም ይሆናል፤ የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግር ጫማ በዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ሲቆም፥ የዮርዳኖስ ውኃ ይደርቃል፤ ከላይ የሚወርደውም ውኃ ይቆማል።”
14እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ሊሻገሩ ከየድንኳናቸው በወጡ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር። 15እንደ ክረምትና እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እስከ ወሰኑ ሞልቶ ነበርና የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸካሚዎቹ ወደ ዮርዳኖስ በገቡ ጊዜ፥ ታቦቱን የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃዉ ዳር ሲጠልቁ፥ 16ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ እስከ ቀርያትያርም አውራጃ እጅግ ርቆ እንደ ግድግዳ ቆመ፤ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃም ፈጽሞ ደረቀ፤ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ቆሙ። 17የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ የእስራኤል ልጆች ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 3: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in