ወደ ሮሜ ሰዎች 11
11
ለእስራኤል ሕዝብ የእግዚአብሔር ምሕረት
1 #
ፊል. 3፥5። እንግዲህ እላለሁ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? አይደለም፤ እኔ ደግሞ ከአብርሃም ዘር ከብንያም ወገን የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ። 2እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝቡን አልጣላቸውም፤ ኤልያስ እስራኤልን ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በከሰሳቸው ጊዜ መጽሐፍ ያለውን አታውቁምን? 3#1ነገ. 19፥10፤ 14። “አቤቱ፥ ነቢያትህን ገደሉ፤ መሠዊያዎችህንም አፈረሱ፤ እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ነፍሴንም ይሿታል።” 4#1ነገ. 19፥18። የተገለጠለትስ ምን አለው? “ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቻለሁ።” 5እንዲሁም ዛሬ በዚህ ዘመን በጸጋ የተመረጡና በእግዚአብሔር ያመኑ#“በእግዚአብሔር ያመኑ” የሚለው በግሪኩ የለም። ቅሬታዎች አሉ። 6በጸጋ ከጸደቁ ግን በሥራቸው አይደለማ፤ በሥራም የሚጸድቁ ከሆነ ጸጋ ጸጋ አይባልም።
7እንግዲህ ምንድን ነው? እስራኤል የፈለገውን አላገኘም። የተመረጠው ግን አግኝቶአል፤ የቀሩትም ታወሩ። 8#ዘዳ. 29፥4፤ ኢሳ. 29፥10። መጽሐፍ እንዳለ፥ “እስከ ዛሬ ድረስ በዐይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ እግዚአብሔር ደንዛዛ አእምሮን ሰጣቸው።” 9ዳዊትም እንዲህ ብሎአል፥ “ማዕዳቸው በፊታቸው ወጥመድና አሽክላ፥ መሰናከያና ፍዳም ትሁንባቸው። 10#መዝ. 68፥22-23። እንዳያዩ ዐይኖቻቸው ይጨልሙ፤ ዘወትርም ጀርባቸው ይጕበጥ።” 11እንግዲህ እላለሁ፤ ሊወድቁ ተሰናከሉን? አይደለም፤ ነገር ግን እስራኤል ይቀኑ ዘንድ እነርሱ በመሰናከላቸው ለአሕዛብ ድኅነት ሆነ። 12የእነርሱ መሰናከል ለዓለም ባለጸግነት፥ በደላቸውም ለአሕዛብ ባለጸግነት ከሆነ ፍጹምነታቸውማ እንዴት በሆነ ነበር?
ስለ አሕዛብ መዳን
13ለእናንተ ለአሕዛብ እናገራለሁ፤ እኔ ለአሕዛብ ሐዋርያቸው እንደ መሆኔ መጠን መልእክቴን አከብራታለሁ። 14ይህም በዚህ ዘመዶችን አስቀናቸው እንደ ሆነ፥ ከእነርሱ ወገን የሆኑትንም አድን እንደ ሆነ ነው። 15የእነርሱ መውጣት ለዓለም ዕርቅ ከሆነ ይልቁንም መመለሳቸው ምን ይሆን? ከሙታን በመነሣት የሚገኝ ሕይወት ነው። 16እርሾው ቅዱስ ከሆነ ቡሆውም እንዲሁ ቅዱስ ነው፤ ሥርዋ ቅዱስ ከሆነም ቅርንጫፎችዋ እንዲሁ ቅዱሳን ይሆናሉ። 17ከቅርንጫፎችዋ አንዳንዶቹ ቢሰበሩ የዱር ወይራ የሆንህ አንተን በእነርሱ ፋንታ ተከሉ፤ የእነርሱንም ሥርነት አገኘህ፤ እንደ እነርሱም ዘይት ሆንኽ። 18በቅርንጫፎች ላይ አትኵራ፤ ብትኰራ ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ አንተ ሥሩን የምትሸከመው አይደለም። 19ቅርንጫፎችዋ ተሰበሩ፤ በእነርሱም ፋንታ “እኔ የዘይት ቅርንጫፍ ሆንሁ” ትል ይሆናል። 20አላመኑምና ተሰበሩ፤ አንተ ግን ስለ አመንህ ቆመሃል፤ እንግዲህ ፈርተህ ኑር እንጂ ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ። 21እግዚአብሔር በተፈጥሮአቸው ቅርንጫፎች ለነበሩ ለእነዚያ ከአልራራላቸው ለአንተም አይራራልህም፤ 22እንግዲህ የእግዚአብሔርን ርኅራኄውንና ጭካኔውን አስተውል፤ የወደቁትን ቀጣቸው፤ አንተን ግን ይቅር እንዳለህ ብትኖር ማረህ፤ ያለዚያ ግን አንተም ትቈረጣለህ። 23እነርሱም ባለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ ይተከላሉ። እግዚአብሔር ዳግመና ሊተክላቸው ይችላልና። 24አንተ የዱር ወይራ፥ አንተን ስንኳ ከበቀልህበት ቈርጦ ባልበቀልህበት በመልካሙ ዘይት ስፍራ ከተከለህ፥ ይልቁን ጥንቱን ዘይት የነበሩትን እነዚያን በበቀሉበት ስፍራ እንዴት አብልጦ ሊተክላቸው አይችልም?
ስለ እስራኤል መመለስ
25ወንድሞቻችን፥ እና ዐዋቂዎች ነን እንዳትሉ ይህን ምሥጢር ልታውቁ እወዳለሁ፦ አሕዛብ ሁሉ እስኪገቡ ድረስ ከእስራኤል እኩሌቶችን የልብ ድንቍርና አግኝቶአቸዋልና። 26#ኢሳ. 59፥20። ከዚህ በኋላም መላው እስራኤል ይድናሉ፤ መጽሐፍ እንዲህ እንዳለ፥ “አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤ ከያዕቆብም ኀጢአትን ያስወግዳል። 27#ኤር. 31፥33-34። ኀጢአታቸውንም ባራቅሁላቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው።” 28በወንጌል በኩል ስለ እናንተ ጠላቶቻችን ናቸው፤ በምርጫ በኩል ግን ስለ አባቶች ወዳጆች ናቸው። 29በእግዚአብሔር ጸጋና በመጥራቱ ጸጸት የለምና። 30ቀድሞ እናንተ እግዚአብሔርን እንደ አልታዘዛችሁት፥ ዛሬ ግን በእነርሱ አለመታዘዝ ይቅር እንዳላችሁ፥ 31እንዲሁም እናንተ በተማራችሁት ምሕረት እነርሱ ምሕረትን እንዲያገኙ እነርሱ ዛሬ አልታዘዙትም። 32እግዚአብሔር ሁሉን ይቅር ይለው ዘንድ ሁሉን በኀጢአት ውስጥ ዘግቶታልና። 33#ኢሳ. 55፥8። የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፤ ፍርዱንም የሚያውቀው የለም። 34#ኢሳ. 40፥13። “የእግዚአብሔርን ዐሳቡን ማን ያውቃል? ወይስ ማን ተማከረው? 35#ኢዮብ 41፥11። ብድሩን ይከፍል ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ ማን አበደረው?” 36#1ቆሮ. 8፥6። ሁሉ ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱ ነውና፤ ለእርሱም ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይሁን። አሜን።
Currently Selected:
ወደ ሮሜ ሰዎች 11: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in