መጽሐፈ ጥበብ 3
3
ቅዱሳን በእግዚአብሔር ረድኤት እንደሚጠበቁ
1የጻድቃን ነፍስ ግን በእግዚአብሔር እጅ ናት፤ መከራም አያገኛቸውም። 2በሰነፎች ዓይኖች ግን የሞቱ መሰሉ፤ በሞትም ከዚህ ዓለም መውጣታቸው ክፋት እንዳለባቸው ተቈጠረ። 3ሞታቸውም ጥፋት መሰለ፤ እነርሱ ግን በሰላም አሉ። 4በሰው ፊትም ቢፈረድባቸው ተስፋቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ሞት የሌለባት ፍጽምት ሕይወት ናት።
5ጥቂት መከራ ተቀብለው ብዙ ክብር ያገኛሉ። እግዚአብሔር ፈትኗቸው ለእርሱ የተገቡ ሆነው አግኝትዋቸዋልና። 6ወርቅ በከውር እንዲፈተን ፈተናቸው፤ እንደሚቃጠል መሥዋዕትም ተቀበላቸው። 7በሚጐበኙበትም ወራት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ በብርዕ ላይ የወደቀ የእሳት ፍንጣሪ እንዲሰፋ በክብር እየሰፉ ይሄዳሉ። 8አሕዛብን ይገዛሉ፤ በሕዝብም ላይ ይሠለጥናሉ፤ እግዚአብሔርም ለዘለዓለም ይነግሥላቸዋል። 9በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች እውነትን ያውቃሉ፤ ጸጋና ምሕረት ለመረጣቸው ነውና፥ የተገለጠ ጕብኝቱም ለጻድቃኑ ነውና ምእመናን በእርሱ ፍቅር ጸንተው ይኖራሉ።
ክፉዎች በክፋታቸው እንደሚጐዱ
10ክፉዎች ሰዎች ግን እንዳሰቡ ክፉ ፍርድን ያገኛሉ፥ እውነትንም ያቀለሉ ሰዎች ከእግዚአብሔር ራቁ።
11ጥበብንና ተግሣጽን የሚንቁ ሰዎች ጐስቋሎች ናቸው፤ አለኝታቸው ከንቱ ነው፤ ድካማቸውም፥ መከራቸውም ጥቅም የሌለው ነው፤ ሥራቸውም ከንቱ ነው፤ 12ሚስቶቻቸውም ሰነፎች ናቸው፤ ልጆቻቸውም ጠማሞች ናቸው፤ ትውልዳቸውም የተረገመ ነው።
በንጽሕና ስለመኖር
13ነውር የሌለባት፥ የኀጢአት ምንጣፍ የማታውቅ መካን ሴት ብፅዕት ናት፥ ከኀጢአትም የነጻች ናት፥ ይህች እንዲህ ያለችው ሴት ነፍሳት በሚጐበኙበት ጊዜ ፍሬ ታገኛለች። 14የተመረጠች የሃይማኖት ዋጋ ትሰጠዋለችና፥ በሚወደድ በእግዚአብሔርም ቤት ዕድሉ ይሰጠዋልና በእጁ በደልን ያልሠራ፥ በእግአብሔርም ላይ ክፉ ነገርን ያላሰበ ጃንደረባም ብፁዕ ነው። 15የደግ ሰው የድካሙ ፍሬ ክብርና ጌጥ ነው፤ ለዕውቀቱም ሥር ውድቀት የለበትም።
16ያመንዝራዎች ልጆች ግን ከቍጥር የጐደሉ ይሆናሉ። ከሕግ ተላላፊ መኝታ የተወለደ ልጅም ይጠፋል። 17ኑሮአቸውም በምድር ላይ ቢበዛ ምንም አይቈጠርም፤ ሽምግልናቸውም በፍጻሜያቸው የጐሰቈለ ይሆናል። 18ፈጥነውም ቢሞቱ በፍርድ ቀን ተስፋና መጽናናት አይኖራቸውም። 19ለዐመፀኛ ትውልድ ፍጻሜዋ ክፉ ነውና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 3: አማ2000
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in