YouVersion Logo
Search Icon

1 ወደ ጢሞቴዎስ 4

4
1-2መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥ 3እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ። 4እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ 5በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና።
6ስለዚህ ወንድሞችን ብታሳስብ፥ በእምነትና በተከተልኸው በመልካም ትምህርት ቃል የምትመገብ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ። 7ነገር ግን ለዚህ ዓለም ከሚመችና የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ ከሚመስለው ተረት ራቅ። እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ። 8ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል። 9ይህ ቃል የታመነ ሁሉም እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ 10ይህን ለማግኘት እንደክማለንና፥ ስለዚህም እንሰደባለን፤ ይህም ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው።
11-12ይህን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው። 13እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ። 14በትንቢት ከሽማግሌዎች እጅ መጫን ጋር የተሰጠህን፥ በአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል። 15ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር። 16ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in