ኦሪት ዘኊልቊ 21
21
1በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ። 2እስራኤልም ለእግዚአብሔር፦ እነዚህን አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ ብሎ ስእለት ተሳለ። 3እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት። 4ከሖርም ተራራ ከኤዶምያስ ምድር ርቀው ሊዞሩ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ የሕዝቡም ሰውነት ከመንገዱ የተነሣ ደከመ። 5ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ፦ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ። 6እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ። 7ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው፦ በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት። 8ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው። 9ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ። 10የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኦቦትም ሰፈሩ። 11ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ፊት ለፊት ባለችው ምድረ በዳ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል፥ በዒዬዓባሪም ሰፈሩ። 12ከዚያም ተጕዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ። 13ከዚያም ተጕዘው ከአሞራውያን ዳርቻ በሚወጣው ምድረ በዳ ውስጥ በአርኖን ማዶ ሰፈሩ፤ አርኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል ያለ የሞዓብ ዳርቻ ነውና። 14ስለዚህ በእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ፦ ዋሄብ በሱፋ፥ የአርኖንም ሸለቆች፥ 15ወደ ዔር ማደሪያ የሚወርድ በሞዓብም ዳርቻ የሚጠጋ የሸለቆች ፈሳሽ። 16ከዚያም ወደ ብኤር ተጓዙ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ሙሴን፦ ሕዝቡን ሰብስብ ውኃንም እሰጣቸዋለሁ ብሎ የተናገረለት ጕድጓድ ነው። 17በዚያም ጊዜ እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ፦ አንተ ምንጭ ሆይ፥ ፍለቅ፤ እናንተም ዘምሩለት፤ 18በበትረ መንግሥት በበትራቸውም የሕዝብ አዛውንቶች ያጐደጐዱት፥ አለቆችም የቈፈሩት ጕድጓድ። 19ከምድረ በዳም ወደ መቴና ተጓዙ፤ ከመቴናም ወደ ነሃሊኤል፥ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት፥ 20ከባሞትም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ በሞዓብ በረሀ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ። 21-22እስራኤልም፦ በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻና ወደ ወይን ቦታ አንገባም፤ ከጕድጓድም ውኃን አንጠጣም፤ ከምድርህ ዳርቻ እስክንወጣ ድረስ በንጉሥ ጐዳና እንሄዳለን ብለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞችን ላኩ። 23ሴዎንም እስራኤል በምድሩ ላይ ያልፍ ዘንድ እንቢ አለ፤ ሴዎንም ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ እስራኤልንም ለመውጋት ወደ ምድረ በዳ ወጣ፥ ወደ ያሀጽም መጣ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ። 24እስራኤልም በሰይፍ መታው፥ ምድሩንም ከአሮኖን ጀምሮ እስከ አሞን ልጆች እስከ ያቦቅ ድረስ ወረሰ፤ የአሞንም ልጆች ዳርቻ የጸና ነበረ። 25እስራኤልም እነዚህን ከተሞች ሁሉ ወሰደ፤ እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ሁሉ በሐሴቦንና በመንደሮቹ ሁሉ ተቀመጠ። 26ሐሴቦንም የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረ፤ እርሱም የፊተኛውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ምድሩን ሁሉ ከእጁ ወስዶ ነበር። 27ስለዚህ በምሳሌ እንዲህ ተብሎ ተነገረ፦ ወደ ሐሴቦን ኑ። የሴዎን ከተማ ይሠራ፥ ይመሥረት፤ 28እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ወጣ፤ የሞዓብን ዔር፥ የአርኖንን ተራራ አለቆች በላ፤ 29ሞዓብ ሆይ፥ ወዮልህ! የከሞስ ሕዝብ ሆይ፥ ጠፋህ፤ ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፥ ሴቶች ልጆቹንም ለምርኮ፥ ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን ሰጠ። 30ገተርናቸው፤ ከሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ጠፉ፤ ኖፋም እስኪደርሱ እስከ ሜድባ አፈረስናቸው። 31እስራኤልም እንደዚህ በአሞራውያን ምድር ተቀመጡ። 32ሙሴም ሰላዮችን ወደ ኢያዜር ሰደደ፤ መንደሮችዋንም ወሰዱ፥ በዚያም የነበሩትን አሞራውያን አባረሩ። 33ተመልሰውም በበሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ ይወጋቸው ዘንድ ወጣ። 34እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግህ እንዲሁ ታደርግበታለህ አለው። 35እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ መቱ ሰውም አልቀረለትም፤ ምድሩንም ወረሱ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 21: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in