ዘፍጥረት 8
8
1እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና በመርከቧ ውስጥ ከእርሱ ጋር የነበሩትን የዱርና የቤት እንስሳት ሁሉ ዐሰበ፤ በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም ጐደለ። 2የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ ውሃ መስኮቶች ተዘጉ፤ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ። 3ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ አምሳ ቀን በኋላም ጐደለ። 4በሰባተኛው ወር፣ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች። 5ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ እየቀነሰ መጣ፤ በዐሥረኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ።
6ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣ 7ቍራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቍራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። 8ከዚያም በኋላ፣ ኖኅ ውሃው ከምድር ገጽ ጐድሎ እንደ ሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤ 9ነገር ግን ውሃው የምድርን ገጽ ገና እንደ ሸፈነ ስለ ነበር፣ ተመልሳ ኖኅ ወዳለበት መርከብ መጣች፤ እርሱም እጁን ዘርግቶ ተቀበላት፤ ወደ መርከቢቱም አስገባት። 10ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደ ገና ላካት። 11እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ያን ጊዜ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጕደሉን ዐወቀ። 12ሰባት ቀንም ቈይቶ ርግቧን እንደ ገና ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እርሱ አልተመለሰችም።
13ኖኅ በተወለደ በ 601 ኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ። 14ኖኅ በመርከቡ ላይ ያለውን ክዳን አንሥቶ ተመለከተ፤ የመሬቱም ገጽ እንደ ደረቀ አየ። በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች።
15ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን እንዲህ አለው፤ 16“አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ። 17እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ፣ ከአንተ ጋር ያሉትን እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።”
18ኖኅም ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ወጣ። 19እንስሳቱ ሁሉ፣ ወፎችም፣ በምድር የሚንቀሳቀሱ ሁሉ በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ።
20ከዚያም ኖኅ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያው ላይ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ፣ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት ወፎች የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ፤ 21እግዚአብሔርም (ያህዌ) ደስ የሚያሰኘውን መዐዛ አሸተተ፤ በልቡም እንዲህ አለ፤ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም#8፥21 ወይም ስለሆነ በእርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጡራንን ዳግመኛ አላጠፋም።
22“ምድር እስካለች ድረስ፣
የዘር ወቅትና መከር፣
ሙቀትና ቅዝቃዜ
በጋና ክረምት፣
ቀንና ሌሊት፣
አይቋረጡም።”
Dewis Presennol:
ዘፍጥረት 8: NASV
Uwcholeuo
Rhanna
Copi
Eisiau i'th uchafbwyntiau gael eu cadw ar draws dy holl ddyfeisiau? Cofrestra neu mewngofnoda
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.