YouVersion logo
Ikona pretraživanja

ሉቃስ 18

18
ተግታ የለመነችው መበለት ምሳሌነት
1ደቀ መዛሙርቱ ሳይታክቱ ሁልጊዜ መጸለይ እንደሚገባቸው ለማሳየት ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ 2እንዲህም አላቸው፤ “በአንዲት ከተማ የሚኖር እግዚአብሔርን የማይፈራና ሰውን የማያከብር አንድ ዳኛ ነበረ። 3በዚያችው ከተማ የምትኖር አንዲት መበለት ነበረች፤ እርሷም፣ ‘ከባላጋራዬ ጋር ስላለብኝ ጕዳይ ፍረድልኝ’ እያለች ወደ እርሱ ትመላለስ ነበር።
4 “ዳኛውም ለተወሰነ ጊዜ አልተቀበላትም ነበር፤ በኋላ ግን በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ፣ ሰውንም ባላከብር፣ 5ይህች መበለት ስለምትጨቀጭቀኝ እፈርድላታለሁ፤ አለዚያ ዘወትር እየተመላለሰች ታሰለቸኛለች።’ ”
6ጌታም እንዲህ አለ፤ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። 7እግዚአብሔርስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? ከመጠን በላይስ ችላ ይላቸዋልን? 8እላችኋለሁ፤ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆንን?”
የፈሪሳዊውና የቀረጥ ሰብሳቢው ምሳሌነት
9ራሳቸውን እንደ ጻድቃን በመቍጠር ለሚመኩና ሌሎቹን በንቀት ዐይን ለሚመለከቱ ሰዎች እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ 10“ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፣ አንዱ ፈሪሳዊ፣ ሌላው ቀረጥ ሰብሳቢ ነበሩ። 11ፈሪሳዊውም ቆሞ ስለ#18፥11 ወይም ለራሱ ራሱ እንዲህ ይጸልይ ነበር፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ቀማኛ፣ ዐመፀኛ፣ አመንዝራ፣ ይልቁንም እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ባለ መሆኔ አመሰግንሃለሁ፤ 12በሳምንት ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ ዐሥራት አወጣለሁ።’
13 “ቀረጥ ሰብሳቢው ግን በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ አልፈለገም፤ ነገር ግን ደረቱን እየደቃ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ’ ይል ነበር።
14 “እላችኋለሁ፤ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይህኛው በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ጻድቅ ተቈጥሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፤ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይላል።”
ኢየሱስ ከሕፃናት ጋር
18፥15-17 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥13-15ማር 10፥13-16
15ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ ያመጡ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ባዩ ጊዜ ገሠጿቸው። 16ኢየሱስ ግን ሕፃናቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። 17እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።”
ሀብታሙ የአይሁድ አለቃ
18፥18-30 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥16-29ማር 10፥17-30
18ከአይሁድ አለቆች አንዱ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው።
19ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም፤ 20‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።”
21ሰውየውም፣ “እነዚህንማ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” አለው።
22ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ “እንግዲያውስ አንድ ነገር ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ መዝገብ ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።
23ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው በጣም ዐዘነ። 24ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ “ብዙ ሀብት ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው? 25ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”
26ይህን የሰሙ ሰዎችም፣ “ታዲያ፣ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።
27ኢየሱስም፣ “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አለ።
28ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል” አለው።
29ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ለእግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የተወ፣ 30በዚህ ዘመን ብዙ ዕጥፍ፣ በሚመጣውም ዘመን የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”
ኢየሱስ ስለ ሞቱ ዳግመኛ ተናገረ
18፥31-33 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥17-19ማር 10፥32-34
31ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻ ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም ልንወጣ ነው፤ ነቢያት ስለ ሰው ልጅ የጻፉትም ሁሉ ይፈጸማል። 32ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነርሱም ያፌዙበታል፤ ያንገላቱታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል። 33እርሱም በሦስተኛው ቀን ከሙታን ይነሣል።”
34ደቀ መዛሙርቱ ግን ከዚህ ሁሉ የተረዱት አንድም ነገር አልነበረም፤ አባባሉም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለ ምን እንደ ተናገረም አላወቁም።
የዐይነ ስውሩ መፈወስ
18፥35-43 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥29-34ማር 10፥46-52
35ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ በቀረበ ጊዜ፣ አንድ ዐይነ ስውር መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 36ዐይነ ስውሩም ሕዝቡ በዚያ ሲያልፍ ሰምቶ ስለ ሁኔታው ጠየቃቸው። 37እነርሱም፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው” ብለው ነገሩት።
38እርሱም፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ጮኸ።
39ከፊት የሚሄዱ ሰዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ አብዝቶ ጮኸ።
40ኢየሱስም ቆም ብሎ ሰውየውን ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ፤ ወደ እርሱም በቀረበ ጊዜ፣ 41“ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው።
ዐይነ ስውሩም፣ “ጌታ ሆይ፤ ማየት እፈልጋለሁ” አለው።
42ኢየሱስም፣ “እይ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። 43ሰውየውም ወዲያውኑ ማየት ቻለ፤ እግዚአብሔርንም እያከበረ ኢየሱስን ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

Trenutno odabrano:

ሉቃስ 18: NASV

Istaknuto

Podijeli

Kopiraj

None

Želiš li svoje istaknute stihove spremiti na sve svoje uređaje? Prijavi se ili registriraj