ኦሪት ዘፍጥረት 3
3
የሰው አለመታዘዝ
1እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው ከምድር አራዊት ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበር። እባብም ሴቲቱን “እግዚአብሔር በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ አትብሉ ያላችሁ ለምንድን ነው?” አላት። 2ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፥ “በገነት መካከል ካለው ከሚያፈራው ዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ 3ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፦ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፤ አትንኩትም።” 4እባብም ለሴቲቱ አላት፥ “ሞትን አትሞቱም፤ 5ከእርስዋ በበላችሁ ቀን፥ ዐይኖቻችሁ እንዲከፈቱ፥ እንደ እግዚአብሔርም እንደምትሆኑ፥ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።” 6ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ፥ ለዐይንም ለማየት እንደሚያስጐመጅ፥ መልካምንም እንደሚያሳውቅ ባየች ጊዜ፥ ከፍሬው ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ። 7የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፤ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ ዐወቁ፤ አፈሩም፤#“አፈሩም” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ። 8እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ በገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ።
9እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ፥ “አዳም፥ ወዴት አለህ?” አለው። 10አዳምም አለ፥ “በገነት ስትመላለስ ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም።” 11እግዚአብሔርም አለው፥ “ዕራቁትህን እንደሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በውኑ በላህን?” 12አዳምም አለ፥ “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ።” 13እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን፥ “ይህን ለምን አደረግሽ?” አላት። ሴቲቱም አለች፥ “እባብ አሳተኝና በላሁ።”
የእግዚአብሔር ፍርድ
14እግዚአብሔር አምላክም እባቡን አለው፥ “ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ሁሉ፥ ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ሁን ፤ በደረትህና በሆድህም ትሄዳለህ፤ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ አፈርን ትበላለህ። 15በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኰናውን ትነድፋለህ።” 16ለሴቲቱም እግዚአብሔር አላት፥ “ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ከወለድሽም በኋላ ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም ይገዛሻል።” 17እግዚአብሔርም አዳምን አለው፥ “የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ከአዘዝሁህ ከዚያ ዛፍም በልተሃልና ምድር በሥራህ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ 18እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። 19ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራህን ትበላለህ፤ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና።” 20አዳምም ለሚስቱ “ሔዋን” ብሎ ስም አወጣ፤ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። 21እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ አለበሳቸውም።
አዳምና ሔዋን ከገነት እንደ ወጡ
22እግዚአብሔር አምላክም አለ፥ “እነሆ፥ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፥” 23ስለዚህ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ደስታ ከሚገኝባት ገነት#ዕብ. “ኤደን ገነት” ይላል። አስወጣው። 24አዳምንም አስወጣው፤ ደስታ በሚገኝባት በገነት አንጻርም አኖረው፤ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በእጃቸው የያዙ ኪሩቤልን#ዕብ. “ኪሩቤልንና ሰይፍን በኤደን ምሥራቅ አስቀመጠ” ይላል። አዘዛቸው።
Voafantina amin'izao fotoana izao:
ኦሪት ዘፍጥረት 3: አማ2000
Asongadina
Hizara
Dika mitovy
Tianao hovoatahiry amin'ireo fitaovana ampiasainao rehetra ve ireo nasongadina? Hisoratra na Hiditra