ዘፍጥረት 27
27
ይስሐቅ ያዕቆብን ባረከው
1ይስሐቅ አርጅቶ፣ ዐይኖቹ ደክመው ማየት በተሳናቸው ጊዜ፣ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ፣ “ልጄ ሆይ” አለው።
እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።
2ይስሐቅም እንዲህ አለ፤ “ይኸው እኔ አርጅቻለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም 3ስለዚህ የዐደን መሣሪያህን፦ የፍላጻ ኰረጆህንና ቀስትህን ይዘህ ወደ ዱር ሂድ፤ አድነህም አምጣልኝ። 4ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ የምወድደውን ዐይነት ጣዕም ያለው ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ።”
5ይስሐቅ ለልጁ የተናገረውን ርብቃ ትሰማ ስለ ነበር፣ ዔሳው የታዘዘውን ለማምጣት ለዐደን እንደ ወጣ፣ 6ርብቃ ለልጇ ለያዕቆብ እንዲህ አለችው፤ “አባትህ ዔሳውን፣ 7‘ከመሞቴ በፊት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንድመርቅህ፣ ጥሩ ጣዕም ያለው ምግብ እንድበላ አዘጋጅልኝ።’ ሲለው ሰምቻለሁ፤ 8ልጄ ሆይ፤ እንግዲህ የምነግርህን በጥሞና ስማኝ፤ የምልህንም አድርግ። 9ተነሣና ወደ መንጋው ሄደህ ሁለት ፍርጥም ያሉ የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እኔም አባትህ የሚወድደውን ዐይነት ምግብ አዘጋጅለታለሁ፤ 10እርሱም ከመሞቱ በፊት እንዲመርቅህ ይዘህለት ግባና ይብላ።”
11ያዕቆብም እናቱን ርብቃን እንዲህ አላት፤ “ወንድሜ ዔሳው ሰውነቱ ጠጕራም ነው፤ የእኔ ገላ ግን ለስላሳ ነው። 12ታዲያ፣ አባቴ ቢዳስሰኝ እንዳታለልሁት ያውቃል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በምርቃት ፈንታ ርግማን አተርፋለሁ ማለት ነው።”
13እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ የአንተ ርግማን በእኔ ላይ ይድረስ፤ ግድ የለህም፤ እንደ ነገርሁህ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው።
14እርሱም ሄዶ ጠቦቶቹን ለእናቱ አመጣላት፤ እርሷም ልክ አባቱ እንደሚወድደው ዐይነት አጣፍጣ ጥሩ ምግብ አዘጋጀችለት። 15ከዚያም ርብቃ በቤት ያስቀመጠችውን የታላቁን ልጇን የዔሳውን ምርጥ ልብስ አንሥታ ለታናሹ ልጇ ለያዕቆብ አለበሰችው። 16እንዲሁም የዐንገቱን ለስላሳ ክፍል የጠቦቶቹን ቈዳ አለበሰችው። 17ከዚያም ያሰናዳችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራ ለያዕቆብ ሰጠችው።
18ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄዶ፣ “አባቴ ሆይ” አለ፤ ይስሐቅም፣ “እነሆ፤ አለሁ ልጄ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አለው።
19ያዕቆብም አባቱን፣ “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ፤ እስቲ ቀና በልና እንድትመርቀኝ ዐድኜ ካመጣሁት ብላ” አለ።
20ይስሐቅ ልጁን፣ “ልጄ ሆይ፤ ከመቼው ቀንቶህ መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) አሳካልኝ” ብሎ መለሰለት።
21ይስሐቅም ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ አንተ በርግጥ ልጄ ዔሳው መሆንህን እንዳውቅ፣ እስቲ ቀረብ በልና ልዳብስህ” አለው።
22ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ተጠጋ፤ አባቱም በእጁ እየዳሰሰው፣ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፤ እጆቹ ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለ። 23እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ስለ ሆኑ፣ ይስሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማወቅ አልቻለም፤ ስለዚህ ባረከው። 24ይስሐቅም፣ “በርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “አዎን፤ ነኝ” ብሎ መለሰ።
25ከዚያም፣ “በል እንግዲህ ልጄ፤ እንድመርቅህ፣ ዐድነህ ካመጣኸው አቅርብልኝና ልብላ” አለው።
ያዕቆብም ምግቡን ለአባቱ አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም አመጣለት፤ እርሱም በላ፤ ጠጣም። 26ከዚያም አባቱ ይስሐቅ፣ ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ እስቲ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው።
27ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው፤ ይስሐቅ የያዕቆብን ልብስ ካሸተተ በኋላ እንዲህ ብሎ መረቀው፤
“እነሆ፤ የልጄ ጠረን፣
እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ባረከው፣
እንደ መስክ መዐዛ ነው።
28እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሰማይን ጠል፣
የምድርንም በረከት፣
የተትረፈረፈ እህልና የወይን ጠጅ ይስጥህ።
29መንግሥታት ይገዙልህ፤
ሕዝቦችም ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤
የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤
የእናትህም ልጆች ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤
የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤
የሚባርኩህ የተባረኩ ይሁኑ።”
30ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃ፣ ያዕቆብ ገና ከአባቱ ዘንድ ሳይወጣ ወዲያውኑ፣ ወንድሙ ዔሳው ከዐደን ተመለሰ። 31እርሱም ደግሞ ጣፋጭ ምግብ በማዘጋጀት ለአባቱ አቅርቦ፣ “አባቴ ሆይ፤ እንድትመርቀኝ፣ እስቲ ቀና በልና ካደንሁት ብላ” አለው።
32አባቱ ይስሐቅም፣ “አንተ ደግሞ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔማ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው።
33በዚህ ጊዜ ይስሐቅ ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ፣ “ታዲያ ቀደም ሲል ዐድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? አንተ ከመምጣትህ በፊት በልቼ መረቅሁት፤ እርሱም በርግጥ የተባረከ ይሆናል” አለው።
34ዔሳው የአባቱን ቃል ሲሰማ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ አለቀሰ፤ አባቱንም፣ “አባቴ ሆይ፤ እኔንም ደግሞ እባክህ መርቀኝ” አለው።
35ይስሐቅም፣ “ወንድምህ መጥቶ አታልሎኝ ምርቃትህን ወስዶብሃል” አለው።
36ዔሳውም፣ “ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ” አለ። ቀጥሎም፣ “ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ብሎ ጠየቀ።
37ይስሐቅም ለዔሳው፣ “በአንተ ላይ የበላይነት እንዲኖረው፣ ወንድሞቹ ሁሉ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ፣ እህሉ፣ የወይን ጠጁም የተትረፈረፈ እንዲሆንለት መርቄዋለሁ። ታዲያ ልጄ፣ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?” ሲል መለሰለት።
38ዔሳውም አባቱን፣ “አባቴ ሆይ፤ ምርቃትህ ይህችው ብቻ ናትን? እባክህ አባቴ፣ እኔንም መርቀኝ” አለው፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።
39አባቱ ይስሐቅም እንዲህ ሲል መለሰለት፤
“መኖሪያህ
ከምድር በረከት፣
ከላይም ከሰማይ ጠል የራቀ ይሆናል፤
40በሰይፍ ትኖራለህ፤
የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ።
አምርረህ በተነሣህ ጊዜ ግን፣
ቀንበሩን ከጫንቃህ ላይ፣
ወዲያ ትጥላለህ።”
ያዕቆብ ወደ ላባ ሸሸ
41አባቱ ያቆብን ስለ መረቀው፣ ዔሳው በያዕቆብ ላይ ቂም ያዘ፤ በልቡም፣ “ግድ የለም፤ የአባቴ መሞቻው ተቃርቧል፤ ከልቅሶው በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድላለሁ” ብሎ ዐሰበ።
42ርብቃ፣ ታላቁ ልጇ ዔሳው ያሰበው በተነገራት ጊዜ ታናሹን ልጇን ያዕቆብን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ጊዜ እየጠበቀ ነው፤ 43አሁንም፣ ልጄ ሆይ፤ እኔ የምልህን አድርግ፤ በካራን ምድር ወደሚኖረው ወደ ላባ ቶሎ ሽሽ። 44የወንድምህ ቍጣ እስከሚበርድ እዚያው ቈይ፤ 45ነገር ግን ቍጣው በርዶለት ያደረግህበትን ከረሳ በኋላ፣ እንድትመለስ እልክብህና ትመጣለህ። ሁለታችሁንም በአንድ ቀን ለምን ልጣ?”
46ከዚያም ርብቃ ይስሐቅን፣ “ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም ከዚሁ አገር ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ” አለችው።
Kasalukuyang Napili:
ዘፍጥረት 27: NASV
Haylayt
Ibahagi
Kopyahin
Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.