ዘፍጥረት 32
32
ያዕቆብ፣ ወንድሙን ዔሳውን ሊገናኝ ተዘጋጀ
1ያዕቆብም ጕዞውን ቀጠለ፤ የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መላእክት ተገናኙት፤ 2ባያቸውም ጊዜ፣ “ይህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰፈር ነው” አለ፤ የዚያንም ቦታ ስም መሃናይም#32፥2 መሃናይም ማለት ሁለት ጐራ ማለት ነው። አለው።
3ያዕቆብም በኤዶም አገር ሴይር በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ዔሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤ 4እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፤ “ጌታዬን ዔሳውን እንዲህ ትሉታላችሁ፤ ‘አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ብሏል በሉት፤ “ከላባ ዘንድ ተቀምጬ እስከ አሁን ድረስ እዚያው ኖርሁ፤ 5ከብቶች፣ አህዮች፣ የበግና የፍየል መንጎች እንደዚሁም የወንድና የሴት አገልጋዮች አሉኝ፤ አሁንም ይህን መልእክት ለጌታዬ መላኬ በጎ ፈቃድህን እንዳገኝ በማሰብ ነው።” ’ ”
6የተላኩትም ሰዎች ወደ ያዕቆብ ተመልሰው፣ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ሊቀበልህ በመምጣት ላይ ነው፤ አራት መቶ ሰዎችም አብረውት አሉ” አሉት። 7ያዕቆብም በታላቅ ፍርሀትና ጭንቀት ተውጦ፣ አብረውት የነበሩትን ሰዎች ሁለት ቦታ#32፥7 ወይም ጐራ፤ በ10 ላይ ያለውም እንዲሁ፤ ከፈላቸው፤ በጎቹን፣ ፍየሎቹን፣ ከብቶቹንና ግመሎቹን ሁለት ቦታ ከፈላቸው። 8“ዔሳው መጥቶ በአንደኛው ላይ አደጋ ቢጥል፣ ሌላው ክፍል#32፥8 ወይም ጐራ ሊያመልጥ ይችላል” ብሎ አስቦ ነበር።
9ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ፣ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ (ኤሎሂም) ሆይ፤ ‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እኔም በጎ ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ 10እኔ ባሪያህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ላይ ከነበረው በትር በስተቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ሰራዊት ሆኛለሁ። 11ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ መጥቶ እኔንም ሆነ እነዚህን እናቶች ከነልጆቻቸው ያጠፋናል ብዬ ፈርቻለሁና፤ 12ነገር ግን፣ አንተ ራስህ፣ ‘አበለጽግሃለሁ፤ ዘርህንም ሊቈጠር እንደማይቻል እንደ ባሕር አሸዋ አበዛዋለሁ’ ብለኸኛል።”
13በዚያችም ሌሊት ያዕቆብ እዚያው ዐደረ፤ ካለው ሀብት ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻ እነዚህን መረጠ፦ 14ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችና ሃያ አውራ ፍየሎች፣ ሁለት መቶ እንስት በጎችና ሃያ አውራ በጎች፣ 15ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎች ከነግልገሎቻቸው፣ አርባ ላሞችና ዐሥር ኮርማዎች፣ ሃያ እንስት አህዮችና ዐሥር ተባት አህዮች። 16እነዚህንም በየመንጋው ለይቶ፣ የሚነዷቸውን ጠባቂዎች መደበላቸው፤ ጠባቂዎቹንም፣ “እናንተ ቀድማችሁኝ ሂዱ፣ መንጋዎቹንም አራርቃችሁ ንዷቸው” አላቸው።
17ቀድሞ የሚሄደውንም እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ዔሳው አግኝቶህ፣ ‘የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? የምትነዳውስ ይህ ሁሉ ከብት የማን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፣ 18‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው፤ ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደዳቸው ናቸው፤ እርሱም ከበስተ ኋላችን እየመጣ ነው’ ብለህ ንገረው።”
19እንዲሁም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና መንጎችን የሚነዱትን ሌሎቹንም ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዔሳውን ስታገኙት ይህንኑ ትነግሩታላችሁ፤ 20በተለይም ‘አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን እየመጣ ነው’ ማለትን አትዘንጉ።” ይህንም ያዘዘው፣ “ዔሳው ከእኔ ጋር ከመገናኘቱ በፊት እጅ መንሻዬ አስቀድሞ ቢደርሰው ምናልባት ልቡ ይራራና በሰላም ይቀበለኛል” ብሎ ስላሰበ ነበር። 21ስለዚህ የያዕቆብ እጅ መንሻ ከእርሱ አስቀድሞ ተላከ፤ እርሱ ራሱ ግን እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ዐደረ።
ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር የገጠመው ትግል
22በዚያች ሌሊት ያዕቆብ ተነሣ፤ ሁለቱን ሚስቶቹን እንዲሁም ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና ዐሥራ አንድ ልጆቹን ይዞ በያቦቅ መልካ ተሻገረ። 23ወንዙን አሻግሮ ከሸኛቸው በኋላ፣ ጓዙን ሁሉ ሰደደ። 24ያዕቆብ ግን ብቻውን እዚያው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው ዐደረ። 25ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ፣ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ በግብግቡም የያዕቆብ ጭን ከመጋጠሚያው ላይ ተናጋ። 26በዚያን ጊዜ ሰውየው፣ “እንግዲህ መንጋቱ ስለሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው።
ያዕቆብም፣ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው።
27ሰውየውም፣ “ስምህ ማን ነው?” አለው።
እርሱም፣ “ያዕቆብ ነው” አለ።
28ሰውየውም፣ “ከእግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል#32፥28 እስራኤል ማለት ከእግዚአብሔር ታገለ ማለት ነው። እንጂ፣ ያዕቆብ አይባልም” አለው።
29ያዕቆብም፣ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው።
ሰውየውም፣ “ስሜን ለማወቅ ለምን ፈለግህ?” አለው፤ በዚያም ስፍራ ባረከው።
30ስለዚህ ያዕቆብ፣ “እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት ለፊት አይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል፣ የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል#32፥30 ጵኒኤል ማለት የእግዚአብሔር ፊት ማለት ነው። አለው።
31ጵኒኤልንም#32፥31 በዕብራይስጥ ጵኑኤል ማለት ሲሆን፣ የጵኒኤል አማራጭ ትርጕም ነው። እንዳለፈ ፀሓይ ወጣችበት፤ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። 32ከዚህም የተነሣ የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ ሹልዳን ከጭኑ ጋር የሚያገናኘውን ሥጋ አይበሉም፤ ምክንያቱም በጭኑ መጋጠሚያ ላይ ያለው የያዕቆብ ሹልዳ ተነክቶ ነበር።
Kasalukuyang Napili:
ዘፍጥረት 32: NASV
Haylayt
Ibahagi
Kopyahin
Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.