ዘፍጥረት 43
43
የዮሴፍ ወንድሞች ዳግመኛ ወደ ግብፅ መሄዳቸው
1ራቡ አሁንም በምድሪቱ ላይ እንደ ጸና ነበር፤ 2ከግብፅ ያመጡትንም እህል በልተው ከጨረሱ በኋላ፣ አባታቸው “እስቲ እንደ ገና ወርዳችሁ፣ ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው።
3ይሁዳ ግን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎ በጥብቅ አስጠንቅቆናል፤ 4ወንድማችን ከእኛ ጋር እንዲወርድ ከፈቀድህ ወደዚያ ሄደን እህል እንሸምትልሃለን፤ 5እርሱን የማትልከው ከሆነ ግን እኛም ወደዚያ አንወርድም፤ ያም ሰው፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎናል።”
6እስራኤልም፣ “ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለዚያ ሰው በመንገር ለምን ይህን ችግር እንዲደርስብኝ አደረጋችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
7እነርሱም፣ “ሰውየው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተ ሰባችን አጥብቆ ጠየቀን፤ እንደ ገናም ‘አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ?’ ሲል ጠየቀን። እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው። ታዲያ፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደዚህ እንድትመጡ’ እንደሚል እንዴት ማወቅ እንችል ነበር?” ብለው መለሱለት።
8ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው “ልጁን ከእኔ ጋር ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፤ ይህ ከሆነ፣ አንተም፣ እኛም፣ ልጆቻችንም አንሞትም፤ እንተርፋለን። 9ስለ ልጁ ደኅንነት እኔ ራሴ ኀላፊ ነኝ፤ ስለ እርሱም በግል ተጠያቂ እሆናለሁ፤ እርሱንም በደኅና መልሼ ባላመጣውና እዚህ በፊትህ ባላቆመው ለዘላለም በደለኛው እኔ ልሁን። 10ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ፣ እስካሁን ሁለት ጊዜ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።”
11ከዚህ በኋላ አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፤ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ፤ ምድሪቱ ከምታፈራው ምርጥ ነገሮች ጥቂት በለሳን፣ ጥቂት ማር፣ ሽቱ፣ ከርቤ፣ ተምርና ለውዝ በየስልቻችሁ ይዛችሁ ለዚያ ሰው እጅ መንሻ ውሰዱለት። 12በየስልቾቻችሁ አፍ ላይ የተገኘውን ብር መመለስ ስላለባችሁ፣ ዕጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ ያ በየስልቾቻችሁ ውስጥ የተገኘው ብር ምናልባት በስሕተት የመጣ ሊሆን ይችላል። 13ወንድማችሁንም ይዛችሁ ወደ ሰውየው በቶሎ ሂዱ። 14ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ይዛችሁ ለመመለስ እንድትችሉ ሁሉን የሚችል#43፥14 ዕብራይስጡ ኤልሻዳይ ይላል። አምላክ በምሕረቱ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እንግዲህ ልጆቼንም ባጣ ምን አደርጋለሁ፤ ያመጣውን እቀበላለሁ።”
15ሰዎቹም እጅ መንሻውን፣ የብሩን ዕጥፍ እንዲሁም ብንያምን ይዘው ተነሡ፤ ወደ ግብፅም በፍጥነት ወረዱ፤ ዮሴፍም ፊት ቀረቡ። 16ዮሴፍ ብንያምን ከወንድሞቹ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ፣ “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ይዘሃቸው ሂድ፤ ዛሬ ቀትር ላይ አብረውኝ ስለሚበሉ ፍሪዳ ተጥሎ ምሳ ይዘጋጅ” አለው።
17አዛዡም ዮሴፍ የነገረውን አደረገ፤ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው። 18ሰዎቹም ወደ ዮሴፍ ቤት በመወሰዳቸው ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ወደዚህ የመጣነው፣ ቀደም ሲል እዚህ መጥተን ስንመለስ በየስልቾቻችን ውስጥ ተመልሶ በተጨመረው ብር ሰበብ ነው። ሰውየው ጥቃት ሊፈጽምብን፣ አስገድዶ ባሮቹ ሊያደርገንና አህዮቻችንን ሊቀማን ይፈልጋል” ብለው ሠጉ።
19ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥ ቀርበው፣ በቤቱ መግቢያ ላይ አነጋገሩት፤ 20“እንዲህም አሉት፤ ጌታችን ሆይ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤ 21ነገር ግን ለዐዳር በሰፈርንበት ቦታ የየስልቾቻችንን አፍ ስንከፍት፣ እያንዳንዳችን በስልቾቻችን አፍ ላይ፣ ብራችንን ሙሉውን አገኘነው። ገንዘቡንም ይኸው መልሰን ይዘን መጥተናል። 22አሁንም እህል መሸመቻ የሚሆነን ተጨማሪ ብር ይዘን መጥተናል፤ ያኔ ገንዘቡን በየስልቾቻችን ውስጥ ማን መልሶ እንዳስቀመጠው ግን አናውቅም” አሉት።
23የቤቱ አዛዥም፣ “አይዟችሁ አትፍሩ፤ በየስልቾቻችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ገንዘብ የሰጣችሁ የእናንተም የአባቶቻችሁም አምላክ (ኤሎሂም) ነው፤ እኔ እንደ ሆንሁ ብሩን ተቀብያለሁ” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ አገናኛቸው።
24የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው። 25ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነግሯቸው ስለ ነበር፣ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ።
26ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ ያመጧቸውን እጅ መንሻዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት። 27ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፤ ከዚያም “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው።
28እነርሱም መልሰው፣ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው” በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው በአክብሮት እጅ ነሡት።
29ዮሴፍ በዐይኑ ሲቃኝ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየና፣ “ያ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ብንያምንም፣ “ልጄ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይባርክህ” አለው። 30ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ በጥልቅ ስለ ተነካ፣ ፈጥኖ ከፊታቸው ገለል አለ፤ ሰወር ያለ ቦታም ፈልጎ፣ ዕልፍኙ ውስጥ አለቀሰ።
31ፊቱን ከታጠበ በኋላ ተመልሶ፣ ስሜቱን በመቈጣጠር፣ “ማእድ ይቅረብ” አለ።
32ለዮሴፍ ለብቻው ቀረበለት፤ ለወንድሞቹም ለብቻቸው ቀረበላቸው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ግብፃውያን ደግሞ ሌላ ገበታ ቀረበላቸው፤ ምክንያቱም ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር አብሮ መመገብን እንደ ጸያፍ ይቈጥሩት ነበር። 33ወንድማማቾቹ ከበኵሩ እስከ ታናሹ እንደየዕድሜያቸው በዮሴፍ ፊት በተርታ ተቀምጠው ነበር፤ በመገረምም እርስ በርሳቸው ተያዩ። 34ከዮሴፍ ገበታ ላይ እየተነሣ ለእያንዳንዳቸው ምግብ ሲቀርብ፣ የብንያም ድርሻ ከሌሎቹ አምስት ዕጥፍ ነበር። እነርሱም እንዲህ ባለ ሁኔታ አብረውት ተደሰቱ፤ እስኪረኩም ጠጡ።
Kasalukuyang Napili:
ዘፍጥረት 43: NASV
Haylayt
Ibahagi
Kopyahin
Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.