Logo ng YouVersion
Hanapin ang Icon

ዘፍጥረት 47

47
1ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ፣ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው ከከነዓን አገር መጥተው በጌሤም ሰፍረዋል” አለው። 2ከወንድሞቹም መካከል አምስቱን መርጦ፣ ፈርዖን ፊት አቀረባቸው።
3ፈርዖን የዮሴፍን ወንድሞች፣ “ሥራችሁ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም ፈርዖንን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ልክ እንደ አባቶቻችን ከብት አርቢዎች ነን” አሉት፤ 4ደግሞም፣ “በከነዓን ምድር ራቡ እጅግ የጸና በመሆኑ በጎችና ፍየሎች የሚሰማሩበት በማጣታቸው፣ ለጊዜው እዚህ ለመኖር መጥተናል፤ አሁንም ባሮችህ በጌሤም ምድር እንድንኖር እንድትፈቅድልን እንለምንሃለን” አሉት።
5ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “አባትህና ወንድሞችህ ወደ አንተ መጥተዋል፤ 6የግብፅ ምድር እንደ ሆነ በእጅህ ነው፤ አባትህንና ወንድሞችህን ምርጥ በሆነው ምድር አስፍራቸው፤ በጌሤም ይኑሩ። ከመካከላቸው ልዩ ችሎታ ያላቸው መኖራቸውን የምታውቅ ከሆነ፣ የከብቶቼ ኀላፊዎች አድርጋቸው።”
7ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን ቤተ መንግሥት አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቀረበው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ከመረቀው#47፥7 ወይም ሰላምታ ካቀረበ በኋላ 8ፈርዖን፣ “ለመሆኑ ዕድሜህ ምን ያህል ነው?” ሲል ያዕቆብን ጠየቀው።
9ያዕቆብም ለፈርዖን፣ “በምድር ላይ በእንግድነት ያሳለፍሁት ዘመን 130 ዓመት ነው፤ ይህም አባቶቼ በእንግድነት ከኖሩበት ዘመን ጋር ሲነጻጸር ዐጭር ነው፤ ችግር የበዛበትም ነበር” ሲል መለሰለት። 10ከዚያም ያዕቆብ ፈርዖንን መርቆ፣ ተሰናብቶት ወጣ።
11ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን በግብፅ እንዲኖሩ አደረገ፤ ፈርዖን በሰጠውም ትእዛዝ መሠረት ምርጥ ከሆነው ምድር ራምሴን በርስትነት ሰጣቸው። 12ዮሴፍም ለአባቱ፣ ለወንድሞቹና ለመላው የአባቱ ቤተ ሰዎች በልጆቻቸው ቍጥር ልክ ቀለብ እንዲሰፈርላቸው አደረገ።
የራቡ ዘመንና የዮሴፍ አመራር
13በመላው ምድር እህል ባለመኖሩ ራቡ እየጸና ሄደ፤ ከዚህ የተነሣም ግብፅና ከነዓን በራብ እጅግ ተጐዱ፤ 14ዮሴፍ የግብፅና የከነዓን ሰዎች እህል በመሸመት የከፈሉትን ገንዘብ ሁሉ ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት አስገባ። 15የግብፅና የከነዓን ሕዝቦችም ገንዘባቸው ባለቀ ጊዜ፣ ግብፃውያን ሁሉ ወደ ዮሴፍ ቀርበው፣ “የምንበላው እህል ስጠን፤ ገንዘባችን አልቆብናል፤ ዐይንህ እያየ እንዴት በራብ እንለቅ?” አሉት።
16ዮሴፍም፣ “ከብቶቻችሁን አምጡ፤ ገንዘባችሁ ካለቀ በከብቶቻችሁ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። 17ስለዚህ ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸው፣ በበጎቻቸው፣ በፍየሎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ለውጥ እህል ሰጣቸው። በከብቶቻቸው ልዋጭ ባገኙት ምግብ የዚያን ዓመት ራብ እንዲወጡት አደረገ።
18ያም ዓመት ካለፈ በኋላ ሕዝቡ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዮሴፍ መጥተው እንዲህ አሉት፣ “እንግዲህ ከጌታችን የምንሰውረው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችን አልቋል፤ ከብቶቻችንንም አስረክበንሃል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው፣ ከመሬታችንና ከእኛ ከራሳችን በስተቀር አንዳች ነገር የለም። 19ታዲያ፣ እያየኸን እንዴት እንለቅ? መሬታችንስ ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንና መሬታችንን ውሰድና በለውጡ እህል ስጠን፤ እኛ የፈርዖን ገባሮች እንሁን፤ መሬታችንም የእርሱ ርስት ይሁን፤ እኛም እንዳንሞት መሬታችንም ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው ዘር ስጠን።”
20ስለዚህ ዮሴፍ የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ራቡም እጅግ ስለ ጸናባቸው ግብፃውያን ሁሉ አንዳቸውም ሳይቀሩ መሬታቸውን ሸጡ፤ ምድሪቱም የፈርዖን ርስት ሆነች። 21ዮሴፍም የግብፅን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር#47፥21 ከኦሪተ ሳምራውያንና ከሰብዓ ሊቃናት ጋር ተመሳሳይ ሲሆን (ቩልጌትንም ይመ)፣ የማሶሬቲኩ ጽሑፍ ግን ሕዝቡን ወደ ከተሞች አጋዘ ይለዋል። የፈርዖን ገባር አደረገው። 22ሆኖም ዮሴፍ የካህናቱን መሬት አልገዛም፤ ምክንያቱም ካህናቱ ከፈርዖን ቋሚ ድርጎ ስለሚያገኙና ፈርዖን ከሚሰጣቸው ድርጎ በቂ ምግብ ስለ ነበራቸው ነው፤ ከዚህም የተነሣ መሬታቸውን አልሸጡም።
23ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፣ ዛሬ እናንተንም መሬታችሁንም ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁና ይህን ዘር ወስዳችሁ በመሬት ላይ ዝሩ። 24መከሩ በሚሰበሰብበት ጊዜ ግን ከአምስት እጅ አንዱን ለፈርዖን ታስገባላችሁ፤ ከአምስት እጅ አራቱን ደግሞ ለመሬታችሁ ዘር፣ እንዲሁም ለራሳችሁ፣ ለቤተ ሰቦቻችሁና ለልጆቻችሁ ምግብ ታደርጉታላችሁ።”
25እነርሱም፣ “እንግዲህ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤ በጌታችን ፊት ሞገስ ካገኘን፣ ለፈርዖን ገባሮች እንሆናለን” አሉት።
26ስለዚህ ዮሴፍ የምርቱ አንድ አምስተኛ ለፈርዖን እንዲገባ የሚያዝ የመሬት ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ይሠራበታል። በዚያን ጊዜ በፈርዖን እጅ ያልገባው መሬት የካህናቱ ብቻ ነበር።
27በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በግብፅ አገር በጌሤም ይኖሩ ነበር፤ በዚያም ሀብት ንብረት ዐፈሩ፤ ቍጥራቸውም እጅግ እየበዛ ይሄድ ጀመር።
28ያዕቆብ በግብፅ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ዕድሜውም አንድ መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነበር። 29እስራኤልም የሚሞትበት ጊዜ መቃረቡን እንደ ተረዳ ልጁን ዮሴፍን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ እጅህን በጭኔ ላይ አኑረህ፣ በጎነትንና ታማኝነትን ልታደርግልኝ ቃል ግባልኝ፤ በምሞትበት ጊዜ በግብፅ አትቅበረኝ፤ 30እኔም ከአባቶቼ ጋር ሳንቀላፋ፣ ከግብፅ አውጥተህ እነርሱ በተቀበሩበት ቦታ ቅበረኝ።”
ዮሴፍም፣ “እሺ፣ እንዳልከኝ አደርጋለሁ” አለ።
31ያዕቆብም፣ “በል ማልልኝ” አለው። ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በዐልጋው ራስጌ ላይ ሆኖ ጐንበስ አለ።#47፥31 ወይም እስራኤልም በዐልጋው ራስጌ በኩል ሰገደ

Kasalukuyang Napili:

ዘፍጥረት 47: NASV

Haylayt

Ibahagi

Kopyahin

None

Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in