ኦሪት ዘፍጥረት 21
21
የይስሐቅ ልደት
1እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሣራን ጐበኛት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት። 2ሣራም ፀነሰች፤ እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ወለደችለት። 3አብርሃምም ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው። 4አብርሃምም ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር እንዳዘዘው በስምንተኛው ቀን ገረዘው። 5አብርሃምም ልጁ ይስሕቅ በተወለደለት ጊዜ መቶ ዓመቱ ነበረ። 6ሣራም፥ “እግዚአብሔር ደስ አሰኘኝ፤ ይህን የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ደስ ይሰኛልና” አለች። 7ደግሞም ሣራ “በእርጅናዋ የወለደችውን ሕፃን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው?” አለች። 8ሕፃኑም አደገ፤ ጡትንም አስጣሉት፤ አብርሃምም ይስሐቅን ጡት ባስጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣን አደረገ።
የአጋርና የይስማኤል መባረር
9ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ይስማኤልን ከልጅዋ ከይስሐቅ ጋር ሲጫወት አየችው። 10ሣራም አብርሃምን አለችው፥ “ይህችን ባሪያ ከነልጅዋ አባርራት፤ የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና።” 11ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት። 12እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ “ስለዚች አገልጋይህና ስለ ሕፃኑ አትዘን፤ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ፤ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና። 13የባሪያዪቱን ልጅ ደግሞ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ፤ ዘርህ ነውና።” 14አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፤ እንጀራንም ወሰደ፤ የውኃ አቍማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፤ ሕፃኑንም ሰጥቶ አስወጣት፤ እርስዋም ሄደች፤ በዐዘቅተ መሐላም በኩል ባለው ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች። 15ውኃውም ከአቍማዳው አለቀ፤ ሕፃኑንም ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር ጥላው ሄደች፤ 16ልጄ ሲሞት አላየውም ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ እየተመለከተች፥ ፊት ለፊት ተቀመጠች፤ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሕፃኑ ቃሉን አሰምቶ አለቀሰ” ይላል። 17እግዚአብሔርም የሕፃኑን ጩኸት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፥ “አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የልጅሽን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። 18ተነሺ፤ ልጅሽንም አንሺ፤ በእጅሽም አጽኚው፤ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” 19እግዚአብሔርም ለአጋር ዐይንዋን ከፈተላት፤ የውኃ ጕድጓድንም አየች፤ ሄዳም አቍማዳውን በውኃ ሞላች፤ ልጅዋንም አጠጣችው። 20እግዚአብሔርም ከዚያ ሕፃን ጋር ነበረ፤ አደገም፤ በምድረ በዳም ተቀመጠ፤ ቀስተኛም ሆነ። 21በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት።
በአብርሃምና በአቤሜሌክ መካከል የተደረገ ስምምነት
22በዚያ ዘመን አቤሜሌክ፥ ሚዜው አኮዘትና የሠራዊቱ አለቃ ፋኮል ወደ አብርሃም ሄደው አሉት፥ “በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ 23አሁንም በእኔም፥ በልጄም፥ በወገኔም፥ ከእኔም ጋር ባለ ክፉ እንዳታደርግብኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ፤ ነገር ግን በእንግድነት መጥተህ ለአንተ ቸርነት እንዳደረግሁ አንተም ለእኔ፥ ለተቀምጥህባትም ምድር ቸርነትን ታደርጋለህ።” 24አብርሃምም፥ “እሺ እኔ እምላለሁ” አለ። 25አብርሃምም አቤሜሌክን ብላቴኖቹ በቀሙት በውኃ ጕድጓድ ምክንያት ወቀሰው። 26አቤሜሌክም አለ፥ “ይህን ነገር ማን እንዳደረገው አላወቅሁም፤ አንተም ደግሞ ምንም አልነገርኸኝም፤ እኔም ከዛሬ በቀር አልሰማሁም።” 27አብርሃምም በጎችንና ላሞችን አምጥቶ ለአቤሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ። 28አብርሃምም ሰባ#ዕብ. “ሰባት” ይላል። ቄቦች በጎችን ለብቻቸው አቆመ። 29አቤሜሌክም አብርሃምን፥ “ለብቻቸው ያቆምሃቸው እነዚያ ሰባ#ዕብ. “ሰባት” ይላል። ቄቦች በጎች ምንድን ናቸው?” አለው። 30እርሱም፥ “እኔ ይህችን የውኃ ጕድጓድ እንደቈፈርሁ ምስክር ይሆኑልኝ ዘንድ እነዚህን ሰባ ቄቦች በጎች ከእጄ ትወስዳለህ” አለው። 31ስለዚህም ያን ጕድጓድ ዐዘቅተ መሐላ ብሎ ጠራው፤ በዚያ እርስ በርሳቸው ተማምለዋልና። 32በዐዘቅተ መሐላ አጠገብም ቃል ኪዳንን አደረጉ። አቤሜሌክና ሚዜው አኮዞት፥ የሠራዊቱ አለቃ ፋኮልም ተነሥተው ወደ ፍልስጥኤም ምድር ተመለሱ። 33አብርሃምም በዐዘቅተ መሐላ አጠገብ የተምር ዛፍን ተከለ፤ በዚያም የዘለዓለሙን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። 34አብርሃምም በፍልስጥኤም ምድር ብዙ ቀን እንግዳ ሆኖ ተቀመጠ።
Поточний вибір:
ኦሪት ዘፍጥረት 21: አማ2000
Позначайте
Поділитись
Копіювати
Хочете, щоб ваші позначення зберігалися на всіх ваших пристроях? Зареєструйтеся або увійдіть