1 ዜና መዋዕል 10
10
ሳኦል ራሱን ገደለ
10፥1-12 ተጓ ምብ – 1ሳሙ 31፥1-13፤ 2ሳሙ 1፥4-12
1በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ወጉ፤ እስራኤላውያንም ከፊታቸው ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ተወግተው ወደቁ። 2ፍልስጥኤማውያን ሳኦልንና ልጆቹን አጥብቀው አሳደዷቸው፤ የሳኦልንም ልጆች ዮናታንን፣ አሚናዳብንና ሜልኪሳን ገደሉ፤ 3ውጊያው በሳኦል ላይ በረታበት፤ ቀስተኞችም ደርሰው ክፉኛ አቈሰሉት።
4ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፣ “እነዚህ ሸለፈታሞች መጥተው መሣለቂያ እንዳያደርጉኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ” አለው።
ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር ፈቃደኛ አልሆነም፤ ስለዚህ ሳኦል በገዛ ሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 5ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ሲያይ፣ እርሱም በራሱ ሰይፍ ላይ ወድቆ ሞተ። 6ስለዚህ ሳኦልና ሦስት ልጆቹ ሞቱ፤ ቤተ ሰዎቹም ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ።
7በሸለቆው ውስጥ የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ሰራዊቱ መሸሹን፣ ሳኦልና ልጆቹም መሞታቸውን ሲያዩ፣ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ከተሞቹን ያዙ።
8በማግስቱ ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ ሲመጡ፣ ሳኦልና ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው። 9ሳኦልን ከገፈፉ፣ ራሱን ከቈረጡና መሣሪያውንም ከወሰዱ በኋላ፣ ለጣዖቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራቹን እንዲናገሩ ወደ መላው የፍልስጥኤም ምድር መልክተኞችን ላኩ። 10የጦር መሣሪያውን በአማልክታቸው ቤተ ጣዖት አስቀመጡት፤ ራሱንም በዳጎን ቤተ ጣዖት ውስጥ አንጠለጠሉት።
11የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን በሰሙ ጊዜ፣ 12ጀግኖቻቸው ሁሉ ተነሥተው የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳ ወደ ኢያቢስ አመጡ፤ ዐጽማቸውንም ኢያቢስ ውስጥ በሚገኘው ትልቁ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤ ሰባት ቀንም ጾሙ።
13ሳኦል ለእግዚአብሔር ስላልታመነ ሞተ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልጠበቀም፤ ይልቁንም ከሙታን ጠሪ ምክርን ጠየቀ፤ 14ይህን ከእግዚአብሔር አልጠየቀም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት እንዲተላለፍ አደረገ።
Currently Selected:
1 ዜና መዋዕል 10: NASV
ማድመቅ
ኮፒ
አወዳድር
ያጋሩ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.