1 ዜና መዋዕል 11

11
ዳዊት በእስራኤል ላይ ነገሠ
11፥1-3 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥1-3
1እስራኤል ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤ 2በቀደመው ዘመን ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለም እንኳ እስራኤልን በጦርነት የምትመራ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፤ መሪያቸውም ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”
3ስለዚህ የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ንጉሥ ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ገባ። እግዚአብሔር በሳሙኤል አማካይነት በተናገረው መሠረት ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት።
ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል አደረገ
11፥4-9 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥6-10
4ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባለው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ ኢያቡሳውያን 5ዳዊትን፣ “ወደዚህ ፈጽሞ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን የጽዮንን ምሽግ ያዘ፤ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት።
6ዳዊትም፣ “ኢያቡሳውያንን ቀድሞ የሚወጋ ሰው የሰራዊቱ አዛዥ ይሆናል” አለ፤ ስለዚህ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ በመጀመሪያ ወጣ፤ እርሱም አዛዥ ለመሆን በቃ።
7ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ውስጥ አደረገ፤ ከዚህም የተነሣ የዳዊት ከተማ ተባለች። 8ዳዊትም ከሚሎ ጀምሮ የከተማዪቱን ዙሪያ ቅጥር ሠራ፤ ኢዮአብ ደግሞ የቀረውን የከተማዪቱን ክፍል መልሶ ሠራ። 9የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበር፣ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ።
የዳዊት ኀያላን ሰዎች
11፥10-41 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 23፥8-39
10የዳዊት ኀያላን ሰዎች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት መንግሥቱ በምድሪቱ ሁሉ ትሰፋ ዘንድ ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋራ ሆነው ለመንግሥቱ ብርቱ ድጋፍ ሰጡ። 11የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም ይህ ነው፤
ሐክሞናዊው ያሾብዓም የጦር መኰንኖቹ አለቃ#11፥11 ሠላሳ ወይም እንደ አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች፣ ሦስት (እንዲሁም 2ሳሙ 23፥8 ይመ) ይላሉ ነበረ፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ በአንድ ጊዜ ሦስት መቶ ሰው ገደለ።
12ከርሱም ቀጥሎ ከሦስቱ ኀያላን አንዱ የሆነው የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልዔዘር ነው፤ 13እርሱም ፍልስጥኤማውያን ለጦርነት በተሰበሰቡ ጊዜ በፈስደሚም ከዳዊት ጋራ ዐብሮ ነበረ፤ ገብስ በሞላበት የዕርሻ ቦታ ወታደሮቹ ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ 14ይሁን እንጂ በዕርሻው መካከል ቦታ ይዘው ስለ ነበረ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ እግዚአብሔርም ታላቅ ድል ሰጣቸው።
15ከፍልስጥኤማውያን ሰራዊት ጥቂቱ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ሳለ፣ ከሠላሳዎቹ አለቆች ሦስቱ ዳዊትን ለመገናኘት በዓዶላም ዋሻ አጠገብ ወደሚገኘው ወደ ዐለቱ ወረዱ። 16በዚያ ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሰራዊት በቤተ ልሔም ነበረ፤ 17ዳዊትም ውሃ ፈልጎ ነበርና፣ “ከቤተ ልሔም በር አቅራቢያ ከሚገኘው ጕድጓድ የምጠጣው ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ። 18በዚህ ጊዜ ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ በቤተ ልሔም በር አጠገብ ከሚገኘው ጕድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣው ስላልፈለገ በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሰው። 19ከዚያም፣ “ይህን ከማድረግ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ፤ ይህ በሕይወታቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም እንደ መጠጣት አይደለምን?” አለ። ይህን ለማምጣት በሕይወታቸው ቈርጠው ስለ ነበር፣ ዳዊት ሊጠጣው አልፈለገም።
ሦስቱ ኀያላን ሰዎች ያደረጉት ጀብዱ እንዲህ ነበር።
20የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ። እርሱም ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰዎች ገደለ፤ ከዚህም የተነሣ እንደ ሦስቱ ሁሉ ዝነኛ ሆነ። 21ከሦስቱ አንዱ ሆኖ ባይቈጠርም እንኳ፣ ዕጥፍ ክብር አገኘ፤ አዛዣቸውም ሆነ።
22ከቀብጽኤል የመጣውና ታላቅ ጀብዱ የሠራው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ብርቱ ተዋጊ ነበረ። እርሱም እጅግ የታወቁ ሁለት የሞዓብ ሰዎችን ገደለ። እንዲያውም አንድ ጊዜ በረዶ ምድርን በሸፈነበት ቀን ወደ አንድ ጕድጓድ ወርዶ አንበሳ ገደለ። 23ደግሞም ቁመቱ ዐምስት ክንድ#11፥23 2.3 ሜትር ያህል ነው። የሆነ አንድ ግብጻዊ ገደለ፤ ግብጻዊው የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር በእጁ ቢይዝም፣ በናያስ ግን ቈመጥ ይዞ ገጠመው፤ ከግብጻዊው እጅ ጦሩን ነጥቆ በገዛ ጦሩ ገደለው። 24የዮዳሄ ልጅ በናያስ የፈጸመው ጀብዱ ይህ ነበር፤ እርሱም እንደ ሦስቱ ኀያላን ዝነኛ ሆነ። 25ከሠላሳዎቹም ይልቅ የበለጠ ክብር ተጐናጸፈ፤ ይሁን እንጂ ከሦስቱ አንዱ አልነበረም፤ ዳዊትም የክብር ዘቡ አዣዥ አደረገው።
26ኀያላኑም እነዚህ ነበሩ፤
የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፣
የቤተ ልሔሙ የዱዲ ልጅ ኤልያናን፣
27ሃሮራዊው ሳሞት፣
ፍሎናዊው ሴሌስ፣
28የቴቁሔ ሰው የሆነው የዒስካ ልጅ፣
ዒራስ፣ የዓናቶቱ ሰው አቢዔዜር፣
29ኩሳታዊው ሴቦካይ፣
አሆሃዊው ዔላይ፣
30ነጦፋዊው ማህራይ፣
የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፣
31ከብንያም ወገን የጊብዓ ሰው የሆነው የሪባይ ልጅ ኤታይ፣
ጲርዓቶናዊው በናያስ፣
32የገዓስ ሸለቆዎች ሰው የሆነው ኡሪ፣
ዐረባዊው አቢኤል፣
33ባሕሩማዊው ዓዝሞት፣
ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፣
34የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፣
የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፣
35የሃራራዊው የሳኮር ልጅ አሒአም፣
የኡር ልጅ ኤሊፋል፣
36ምኬራታዊው ኦፌር፣
ፍሎናዊው አኪያ፣
37ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፣
የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፤
38የናታን ወንድም ኢዮኤል፣
የሃግሪ ልጅ ሚብሐር፣
39አሞናዊው ጼሌቅ፣
የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ብኤሮታዊው ነሃራይ፣
40ይትራዊው ዒራስ፣
ይትራዊው ጋሬብ፣
41ኬጢያዊው ኦርዮ፣
የአሕላይ ልጅ ዛባድ፣
42የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፤ እርሱም የሮቤላውያንና ዐብረውት ለነበሩት የሠላሳ ሰዎች አለቃ ነበረ።
43የማዕካ ልጅ ሐናን፣
ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፣
44አስታሮታዊው ዖዝያ፣
የአሮዔራዊው የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፣
45የሺምሪ ልጅ ይዲኤል፣
ወንድሙም ቴዳዊው ዮሐ፣
46መሐዋዊው ኤሊኤል፣
የኤልነዓም ልጆች ይሪባይና ዮሻውያ፣
ሞዓባዊው ይትማ፣
47ኤሊኤል፣ ዖቤድና ምጾባዊው የዕሢኤል።

ማድመቅ

ኮፒ

አወዳድር

ያጋሩ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ