1 ዜና መዋዕል 13
13
የታቦቱ መመለስ
13፥1-14 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 6፥1-11
1ዳዊትም ሻለቆችና መቶ አለቆች ከሆኑት የጦር ሹማምቱ ሁሉ ጋራ ተማከረ። 2ከዚያም ለመላው የእስራኤል ማኅበር እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ነገሩ መልካም መስሎ ከታያችሁና የአምላካችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፣ በእስራኤል ግዛት ሁሉ ለሚኖሩ በሩቅም ሆነ በቅርብ ላሉት ለቀሩት ወንድሞቻችን እንዲሁም በየራሳቸው ከተሞችና መሰማሪያዎች የሚኖሩ ካህናትና ሌዋውያን መጥተው ከእኛ ጋራ እንዲሰባሰቡ እንላክባቸው። 3በሳኦል ዘመነ መንግሥት ሳንፈልገው#13፥3 ወይም፣ ችላ ብለን የነበረውን የአምላካችንን ታቦት መልሰን ወደ እኛ እናምጣ”። 4ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ መላው ማኅበር ይህንኑ ለማድረግ ተስማማ።
5ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከቂርያትይዓይሪም ለማምጣት ከግብጽ ወንዝ ከሺሖር ጀምሮ እስከ ለቦ ሐማት#13፥5 ወይም፣ ወይም እስከ መተላለፊያው ድረስ የሰፈሩትን እስራኤላውያን ሁሉ ሰበሰበ። 6ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በኪሩብና በኪሩብ መካከል የተቀመጠውን ስሙም በርሱ የተጠራውን፣ የእግዚአብሔር አምላክን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓይሪም ወደተባለችው ወደ በኣላ ሄዱ።
7የእግዚአብሔርንም ታቦት ከአሚናዳብ ቤት በአዲስ ሠረገላ ላይ አድርገው አመጡት፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም ዖዛና አሒዮ ነበሩ። 8ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሆነው በቅኔና በበገና፣ በመሰንቆና በከበሮ፣ በጸናጽልና በመለከት በሙሉ ኀይላቸው በዓሉን በደስታ ያከብሩ ነበር።
9ወደ ኪዶን ዐውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ አደናቅፏቸው ስለ ነበር፣ ዖዛ ታቦቱን ለመደገፍ እጁን ዘረጋ። 10ታቦቱን በእጁ ስለ ነካ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም በዚያው በእግዚአብሔር ፊት ሞተ።
11የእግዚአብሔር ቍጣ ዖዛን በድንገት ስለ ቀሠፈው ዳዊት ዐዘነ፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ የፔሬዝ ዖዛ ስብራት ተብሎ ይጠራል።
12ዳዊት በዚያ ዕለት እግዚአብሔርን ስለ ፈራ፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት ማምጣት እችላለሁ?” አለ። 13ስለዚህ ታቦቱን ወደ ዳዊት ከተማ በመውሰድ ፈንታ የጋት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው። 14የእግዚአብሔርንም ታቦት በአቢዳራ ቤት ከቤተ ሰቡ ጋራ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም ቤተ ሰቡንና ያለውንም ሁሉ ባረከ።
Currently Selected:
1 ዜና መዋዕል 13: NASV
ማድመቅ
ኮፒ
አወዳድር
ያጋሩ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.