1 ዜና መዋዕል 14
14
የዳዊት ቤትና ቤተ ሰቡ
14፥1-7 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥11-16፤ 1ዜና 3፥5-8
1በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት ቤተ መንግሥት እንዲሠሩ መልክተኞችን፣ ድንጋይ ጠራቢዎችንና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችን ከዝግባ ዕንጨት ጋራ ላከ። 2ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም ሲል መንግሥቱን እጅግ ከፍ ከፍ እንዳደረገለት ተገነዘበ።
3ዳዊት በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ሚስቶች አገባ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወለደ። 4በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ስም ይህ ነው፤ ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣ 5ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ኤሊፋላት፣ 6ኖጋ፣ ናፌቅ፣ ያፍያ፣ 7ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት።
ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረገ
14፥8-17 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥17-25
8ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ፍለጋ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊትም ይህን ሰምቶ ስለ ነበር ሊገጥማቸው ወጣ። 9በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን መጥተው የራፋይምን ሸለቆ ወረሩ። 10ስለዚህም ዳዊት፣ “በፍልስጥኤማውያን ላይ ወጥቼ ልምታቸውን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ።
እግዚአብሔርም፣ “አዎን ውጣ! በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ” ብሎ መለሰለት።
11ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ በኣልፐራሲም#14፥11 በኣልፐራሲም ማለት የሚሰብረው ጌታ ማለት ነው። ወጡ፤ በዚያም ድል አደረጋቸው። ዳዊትም፣ “የጐርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ ሁሉ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በእጄ አፈራረሳቸው” አለ፤ ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም “በኣልፐራሲም” ተባለ። 12ፍልስጥኤማውያን አማልክታቸውን በዚያው ጥለዋቸው ስለ ነበር፣ ዳዊት በእሳት እንዲያቃጥሏቸው አዘዘ።
13ፍልስጥኤማውያን ሸለቆውን እንደ ገና ወረሩ፤ 14ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት “ዙሪያውን ከብበህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት አደጋ ጣልባቸው እንጂ ከኋላቸው በቀጥታ ወደ ላይ አትውጣ፤ 15በሾላው ዐናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ወዲያውኑ ለጦርነት ውጣ፤ ይህም የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቷል ማለት ነውና።” 16ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖን ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መቷቸው።
17ከዚህም የተነሣ የዳዊት ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ እግዚአብሔርም መንግሥታት ሁሉ እንዲፈሩት አደረገ።
Currently Selected:
1 ዜና መዋዕል 14: NASV
ማድመቅ
ኮፒ
አወዳድር
ያጋሩ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.