1 ዜና መዋዕል 15
15
ታቦቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተወሰደ
15፥25–16፥3 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 6፥12-19
1ዳዊት በስሙ በተጠራችው ከተማ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔር ታቦት ቦታ አዘጋጅቶ ድንኳን ተከለ። 2ከዚያም ዳዊት፣ “የእግዚአብሔርን ታቦት እንዲሸከሙና ለዘላለም በፊቱ እንዲያገለግሉ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር፣ የእግዚአብሔርን ታቦት ማንም አይሸከም” ሲል አዘዘ።
3ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ወዳዘጋጀለት ስፍራ እንዲያመጡ እስራኤልን ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰበሰበ።
4የአሮንን ዘሮችና ሌዋውያኑንም በአንድነት ሰበሰበ፤
5ከቀዓት ዘሮች፣
አለቃውን ኡርኤልንና አንድ መቶ ሃያ የሥጋ ዘመዶቹን፤
6ከሜራሪ ዘሮች፣
አለቃውን ዓሣያንና ሁለት መቶ ሃያ የሥጋ ዘመዶቹን፤
7ከጌርሶን ዘሮች፣
አለቃውን ኢዩኤልንና አንድ መቶ ሠላሳ የሥጋ ዘመዶቹን፤
8ከኤሊጻፋን ዘሮች፣
አለቃውን ሸማያንና ሁለት መቶ የሥጋ ዘመዶቹን፤
9ከኬብሮን ዘሮች፣
አለቃውን ኤሊኤልንና ሰማንያ የሥጋ ዘመዶቹን፤
10ከዑዝኤል ዘሮች፣
አለቃውን አሚናዳብንና አንድ መቶ ዐሥራ ሁለት የሥጋ ዘመዶቹን።
11ከዚያም ዳዊት ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን፣ ሌዋውያኑን ኡርኤልን፣ ዓሣያን፣ ኢዩኤልን፣ ሸማያን፣ ኤሊኤልንና አሚናዳብን ጠርቶ፣ 12እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ እናንተ የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች ስለ ሆናችሁ፣ እናንተና ወንድሞቻችሁ ሌዋውያን ራሳችሁን ቀድሱ፤ ከዚያም የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ወዳዘጋጀሁለት ቦታ አምጡ። 13የአምላካችን የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችን ላይ እንዲህ የነደደው እናንተ ሌዋውያኑ ቀድሞም ስላላመጣችሁት ነው፤ እኛም ብንሆን ምን ማድረግ እንዳለብን በታዘዘው መሠረት አልጠየቅነውም።” 14ስለዚህ ካህናቱና ሌዋውያኑ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ለማምጣት ራሳቸውን ቀደሱ። 15ሙሴ በእግዚአብሔር ቃል እንዳዘዘው፣ ሌዋውያኑ የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎች አድርገው ተሸከሙ።
16ዳዊትም በዜማ መሣሪያ፣ ማለትም በመሰንቆ፣ በበገናና በጸናጽል እየታጀቡ የደስታ ዜማዎችን የሚያዜሙ መዘምራንን ከወንድሞቻቸው መካከል እንዲሾሙ ለሌዋውያኑ መሪዎች ነገራቸው።
17ስለዚህ ሌዋውያኑ የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን ሾሙ፤ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፣ ከወንድሞቻቸው ከሜራሪ ዘሮች የቂሳን ልጅ ኤታንን ሾሙ፤ 18ከእነርሱም ጋራ ወንድሞቻቸው በደረጃ ተሾሙ፤ እነርሱም ዘካርያስ#15፥18 ሦስት የዕብራይስጥ ቅጆችና በርካታ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች (እንዲሁም ቍ 20 እና 1ዜና 16፥5 ይመ)፤ በርካታ የዕብራይስጥ ቅጆች የዘካርያስ ልጅ ወይም ዘካርያስ፣ ቤን ይላሉ።፣ ያዝኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ ዑኒን፣ ኤልያብ፣ በናያስ፣ መዕሤያን፣ መቲትያ፣ ኤሊፍሌሁ፣ ሚቅኔያ፣ ደግሞም በር ጠባቂዎቹ አቢዳራ ይዒኤል#15፥18 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም (እንዲሁም ቍ 21) ግን ይዒኤልና ዓዛዝያ ይላል። ነበሩ።
19መዘምራኑ ኤማን፣ አሳፍና ኤታን በናስ ጸናጽል ድምፁን ከፍ አድርገው እንዲያሰሙ ተሾሙ፤ 20ዘካርያስ፣ ዓዝኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ ዑኒ፣ ኤልያብ፣ መዕሤያና በናያስ ደግሞ በአላሞት#15፥20 ምናልባት የዜማ ስም ነው። ቅኝት መሰንቆ ይገርፉ ነበር። 21እንዲሁም መቲትያ፣ ኤሊፍሌሁ፣ ሚቅኔያ፣ አቢዳራ፣ ይዒኤል፣ ዓዛዝያ፣ በሺሚኒት#15፥21 ምናልባት የዜማ ስም ነው። ቅኝት በገና ይደረድሩ ነበር። 22የዝማሬው ኀላፊ ሌዋዊው አለቃ ክናንያ ነበረ፤ ይህን ኀላፊነት የወሰደው በዝማሬ የተካነ ስለ ነበር ነው።
23በራክያና ሕልቃና የታቦቱ በር ጠባቂዎች ነበሩ፤ 24ካህናቱ ሰበኒያ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ናትናኤል፣ ዓማሣይ፣ ዘካርያስ፣ በናያስና አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። አቢዳራ ይሒያ ደግሞ የታቦቱ በር ጠባቂዎች ነበሩ።
25ስለዚህ ዳዊት የእስራኤል ሽማግሌዎችና የሻለቃው አዛዦች የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢዳራ ቤት በደስታ ለማምጣት ሄዱ። 26የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያን እግዚአብሔር ረድቷቸው ስለ ነበር፣ ሰባት ኰርማዎችና ሰባት አውራ በጎች ሠዉ። 27ታቦቱን የተሸከሙት ሌዋውያን ሁሉ፣ መዘምራኑና የመዘምራኑ አለቃ ክናንያ የለበሱትን ዐይነት ከቀጭን በፍታ የተሠራ ልብስ ዳዊትም ለብሶ ነበር፤ እንዲሁም ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ ነበር። 28በዚህ ሁኔታ መላው የእስራኤል ሕዝብ በሆታ ቀንደ መለከትና እንቢልታ እየነፉ፣ ጸናጽል እየጸነጸሉ፣ መሰንቆና በገና እየደረደሩ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አመጡ።
29የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ ሲገባ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡ ዳዊት ሲደሰትና ሲያሸበሽብ ባየችው ጊዜ በልቧ ናቀችው።
Currently Selected:
1 ዜና መዋዕል 15: NASV
ማድመቅ
ኮፒ
አወዳድር
ያጋሩ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.