1 ዜና መዋዕል 20

20
የራባ ከተማ መያዝ
20፥1-3 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 11፥1፤ 12፥29-31
1ነገሥታት ለጦርነት በሚወጡበት በጸደይ ወራት፣ ኢዮአብ የጦር ሰራዊቱን እየመራ ሄዶ የአሞናውያንን አገር አጠፋ፤ ወደ ረባትም ሄዶ ከበባት፤ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። ኢዮአብም ረባትን ወግቶ አፈራረሳት። 2ዳዊት የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ ክብደቱም አንድ መክሊት#20፥2 34 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ወርቅ ነበረ፤ ይህንም በዳዊት ራስ ላይ ጫኑለት፤ እንዲሁም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ። 3በዚያ የነበረውንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ ዶማና መጥረቢያ ይዘው እንዲሠሩ አደረጋቸው። ዳዊት በሌሎቹም የአሞን ከተሞች ሁሉ ይህንኑ አደረገ። ከዚያም ዳዊትና መላው ሰራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ከፍልስጥኤማውያን ጋራ የተደረገ ጦርነት
2፥4-8 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 21፥15-22
4ከዚያም በኋላ ከፍልስጥኤማውያን ጋራ በጌዝር ጦርነት ተደረገ፤ በዚያ ጊዜ ኩሳታዊው ሴቦካይ ከራፋይም ዘር የሆነውን ሲፋይን ገደለ፤ ፍልስጥኤማውያንም ድል ተመቱ።
5ከፍልስጥኤማውያን ጋራ ሌላ ጦርነት ተደረገ፤ የያዒር ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ ውፍረቱ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሚያህለውን የጋት ሰው የሆነውን የጎልያድን ወንድም ላሕሚን ገደለ።
6ደግሞም ጋት ላይ በተደረገ ሌላ ጦርነት፣ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ስድስት ስድስት ጣት በድምሩ ሃያ አራት ጣት የነበሩት አንድ ግዙፍ ሰው ነበረ፤ ይህም እንደዚሁ ከራፋይም ዘር ነበረ። 7እርሱም እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው።
8በጋት የነበሩ የራፋይም ዘሮች እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም በዳዊትና በሰዎቹ እጅ ወደቁ።

ማድመቅ

ኮፒ

አወዳድር

ያጋሩ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ