1 ዜና መዋዕል 21

21
ዳዊት ተዋጊ ሰራዊቱን ቈጠረ
21፥1-26 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 24፥1-25
1ሰይጣን በእስራኤል ላይ ተነሥቶ ዳዊት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲቈጥር አነሣሣው። 2ዳዊትም ኢዮአብንና የሰራዊቱን አዛዦች፣ “ሄዳችሁ ከቤርሳቤህ እስከ ዳን ያሉትን እስራኤላውያን ቍጠሩ፤ ከዚያም ምን ያህል እንደ ሆኑ ዐውቅ ዘንድ ንገሩኝ” አላቸው።
3ኢዮአብ ግን፣ “እግዚአብሔር የእስራኤልን ሰራዊት አሁን ካለው በላይ በመቶ ዕጥፍ ያብዛው፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ ሁሉስ ቢሆኑ የጌታዬ ተገዦች አይደሉምን? ታዲያ ንጉሡ ጌታዬ ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገው? ለምንስ በእስራኤል ላይ በደል ያመጣል?” አለ።
4ይሁን እንጂ የንጉሡ ቃል ኢዮአብን አሸነፈው፤ ስለዚህ ኢዮአብ ወጣ፤ በመላው እስራኤል ከተዘዋወረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 5ኢዮአብም የተዋጊዎቹን ሰዎች ቍጥር ለዳዊት አቀረበ፤ እነዚህም በመላው እስራኤል አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺሕ፣ በይሁዳ ደግሞ አራት መቶ ሰባ ሺሕ ሲሆኑ፣ ሁሉም ሰይፍ መምዘዝ የሚችሉ ነበሩ።
6ኢዮአብ ግን የንጉሡ ትእዛዝ አስጸያፊ ነበረና፣ የሌዊንና የብንያምን ነገድ ጨምሮ አልቈጠረም። 7ይህ ትእዛዝ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤልን ቀጣ።
8ከዚያም ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ባደረግሁት ነገር ታላቅ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ የፈጸምሁትም ታላቅ የስንፍና ሥራ ስለ ሆነ፣ የባሪያህን በደል እንድታስወግድ እለምንሃለሁ” አለ።
9 እግዚአብሔርም የዳዊት ባለራእይ የሆነውን ጋድን እንዲህ አለው፤ 10“ሂድና ዳዊትን እንዲህ ብለው ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ እነሆ፣ ሦስት ምርጫ ሰጥቼሃለሁ፤ በአንተ ላይ አደርግብህ ዘንድ አንዱን ምረጥ።’ ”
11ስለዚህ ጋድ ወደ ዳዊት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘በል እንግዲህ አንዱን ምረጥ፤ 12የሦስት ዓመት ራብ ወይስ የጠላቶችህ ሰይፍ ለሦስት ወር አይሎብህ መጥፋት ወይስ ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ መቅሠፍት በምድሪቱ ላይ ወርዶ የእግዚአብሔር መልአክ እስራኤልን ሁሉ ያጥፋ?’ ለላከኝ ምን እንደምመልስ ወስን።”
13ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ታላቅ ስለ ሆነ፣ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻለኛል፤ በሰው እጅስ አልውደቅ” አለ።
14ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መቅሠፍት ላከ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺሕ ሰው ዐለቀ። 15እንዲሁም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፋ መልአክ ላከ፤ መልአኩ ሊያጠፋትም ሲል እግዚአብሔር አይቶ ስለሚደርሰው ጥፋት ዐዘነ፤ ሕዝቡን የሚያጠፋውንም መልአክ፣ “በቃ! እጅህን መልስ” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።
16ዳዊት ቀና ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔር መልአክ በሰማይና በምድር መካከል ቆሞ አየ፤ መልአኩም በኢየሩሳሌም ላይ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ ነበር፤ ከዚያም ዳዊትና ሽማግሌዎቹ ማቅ እንደ ለበሱ በግምባራቸው ተደፉ።
17ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ተዋጊዎቹ እንዲቈጠሩ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? ኀጢአት የሠራሁትም ሆነ የተሳሳትሁም እኔ ነኝ፤ እነዚህ እኮ በጎች ናቸው፤ ታዲያ እነርሱ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን እንጂ፣ መቅሠፍቱ በሕዝብህ ላይ አይውረድ” አለ።
18ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ እንዲነግረው ጋድን አዘዘው። 19ስለዚህ ዳዊትም ጋድ በእግዚአብሔር ስም በነገረው ቃል ታዝዞ ለመፈጸም ወጣ።
20ኦርና ስንዴ በመውቃት ላይ ሳለ ዘወር ሲል መልአኩን አየ፤ ዐብረውት የነበሩት አራት ወንዶች ልጆቹም ተሸሸጉ። 21ዳዊት ወደ እርሱ እየቀረበ መጣ፤ ኦርናም ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ዳዊትን አየው፤ ከዐውድማውም ወጥቶ መሬት ላይ ለጥ ብሎ በመደፋት ለዳዊት እጅ ነሣ።
22ዳዊትም ኦርናን፣ “በሕዝቡ ላይ የወረደው መቅሠፍት እንዲወገድ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ዐውድማህን ልውሰደው፤ ሙሉውን ዋጋ እከፍልሃለሁ” አለው።
23ኦርናም ዳዊትን፣ “እንዲሁ ውሰደው፤ ጌታዬ ንጉሥ ደስ ያለውን ያድርግ። እነሆ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎቹን፣ ለሚነድደውም ዕንጨት መውቂያ በትሮቹን፣ ስንዴውን ደግሞ ለእህል ቍርባን እንዲሆን እሰጣለሁ፤ ሁሉንም እኔ እሰጣለሁ” አለ።
24ንጉሥ ዳዊት ግን ኦርናን “እንዲህ አይደረግም፤ ሙሉውን ዋጋ እኔ እከፍላለሁ፤ የአንተ የሆነውን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ አልፈልግም፤ ዋጋ ያልከፈልሁበትንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም” ሲል መለሰለት።
25ስለዚህም ዳዊት ለኦርና የቦታውን ዋጋ ስድስት መቶ ሰቅል#21፥25 6.9 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ወርቅ ከፈለ። 26ዳዊትም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት#21፥26 በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት ይባላል። አቀረበ። እግዚአብሔርንም ጠራ፤ እግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ከሰማይ በእሳት መለሰለት።
27ከዚያም እግዚአብሔር ለመልአኩ ተናገረ፤ መልአኩም ሰይፉን ወደ አፎቱ መለሰ። 28በዚያ ጊዜ ዳዊት፣ እግዚአብሔር በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ እንደ መለሰለት ሲያይ፣ በዚያው ቦታ መሥዋዕት ማቅረብ ጀመረ። 29ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳንና የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ በዚያ ጊዜ በገባዖን ኰረብታ ላይ ነበረ። 30ዳዊት የእግዚአብሔርን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ ወደዚያ ሄዶ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ አልቻለም።

ማድመቅ

ኮፒ

አወዳድር

ያጋሩ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ