የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 20

20
ዳዊትና ዮናታን
1ከዚህ በኋላ ዳዊት በአርማቴም ካለችው ከነዋት ዘራማ ሸሽቶ ወደ ዮናታን በመሄድ፣ “ምን አድርጌአለሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ? አባትህ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚፈልገውስ በፊቱ ምን ተገኝቶብኝ ነው?” ሲል ጠየቀው።
2ዮናታንም፣ “ይህስ ከቶ አይሁንብህ፤ አትሞትም! እነሆ፤ አባቴ ትልቅም ይሁን ትንሽ ማንኛውንም ነገር አስቀድሞ ሳይነግረኝ አያደርገውም። ታዲያ አባቴ ይህን ለምን ይደብቀኛል? ነገሩ እንዲህ አይደለም” ብሎ መለሰለት።
3ዳዊት ግን፣ “በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አባትህ በሚገባ ያውቃል፤ እርሱም በልቡ፤ ‘ዮናታን እንዳያዝን ይህን ማወቅ የለበትም’ ብሏል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በነፍስህ እምላለሁ በእኔና በሞት መካከል አንድ ርምጃ ብቻ ቀርቷል” ብሎ ማለ።
4ዮናታንም ዳዊትን፣ “እንዳደርግልህ የምትፈልገውን ማንኛውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው።
5ስለዚህ ዳዊት እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ነገ የወር መባቻ በዓል ስለ ሆነ፣ ከንጉሡ ጋራ ምሳ መብላት ይጠበቅብኛል፤ ነገር ግን እስከ ከነገ ወዲያ ማታ ድረስ ከዱር ልደበቅ፤ 6አባትህ ከፈለገኝ፣ ‘ለቤተ ዘመዶቹ ሁሉ ዓመታዊ መሥዋዕት የሚቀርብ ስለ ሆነ፣ ዳዊት ወደ መኖሪያ ከተማው ወደ ቤተ ልሔም ቶሎ ለመሄድ አጥብቆ ፈቃድ ጠየቀኝ’ ብለህ ንገረው። 7እርሱም ‘መልካም ነው’ ካለ፣ አገልጋይህን የሚያሠጋው የለም፤ ከተቈጣ ግን፣ ክፉ ነገር እንዳሰበብኝ ታረጋግጣለህ። 8አንተ ግን፤ ለአገልጋይህ በጎነትን አሳይ፣ ከአገልጋይህ ጋራ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ገብታችኋልና። እኔ በደለኛ ከሆንሁ፣ አንተው ራስህ ግደለኝ፤ ለምንስ ለአባትህ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ!”
9ዮናታንም፣ “ይህ ከአንተ ይራቅ! አባቴ ክፉ ነገር እንዳሰበብህ ባውቅ ኖሮ እንዴት ሳልነግርህ እቀራለሁ?” አለው።
10ዳዊትም፣ “አባትህ ክፉ ቃል ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?” ብሎ ጠየቀው።
11ዮናታን፣ “በል ና፤ ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው፤ ተያይዘውም ወጡ።
12ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁንብኝ፤ አባቴን ነገ መርምሬ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ሰዓት እልክብሃለሁ፤ ስለ አንተ ያለው አመለካከት በጎ ከሆነም አሳውቅሃለሁ። 13ነገር ግን አባቴ ክፉ አስቦብህ፣ ይህን ሳላሳውቅህ ብቀርና በሰላም እንድትሄድ ባላደርግ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፤ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ። እግዚአብሔር ከአባቴ ጋራ እንደ ነበር እንደዚሁ ከአንተም ጋራ ይሁን። 14አንተም እኔ በሕይወት እስካለሁ ድረስ እንዳልገደል የእግዚአብሔርን በጎነት አድርግልኝ። 15እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ ከምድረ ገጽ በሚደመስስበት ጊዜ እንኳ የበጎነት ሥራህ ከቤተ ሰቤ በፍጹም አይቋረጥ።”
16ስለዚህ ዮናታን፣ “የዳዊትን ጠላቶች እግዚአብሔር ይፋረዳቸው” በማለት ከዳዊት ቤት ጋራ ቃል ኪዳን አደረገ። 17ዮናታን ከፍቅሩ የተነሣ ዳዊት እንደ ገና እንዲምልለት አደረገ፤ ዳዊትን የሚወድደውም እንደ ራሱ አድርጎ ነበርና።
18ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ነገ የወር መባቻ በዓል ነው፤ መቀመጫህ ባዶ ስለሚሆን፣ አለመኖርህ ይታወቃል። 19ከነገ ወዲያ ምሽት ላይ ይህ ችግር በተፈጠረ ዕለት ወደ ተደበቅህበት ስፍራ ሂድና ኤዜል በተባለው ድንጋይ አጠገብ ቈይ። 20እኔም በአንድ ዒላማ ላይ እንደሚያነጣጥር ሰው ወደ ድንጋዩ አጠገብ ሦስት ፍላጻ እወረውራለሁ፤ 21ከዚያም፣ ‘ሂድና ፍላጾቹን አምጣቸው’ ብዬ አንድ ልጅ እልካለሁ፤ ልጁንም፣ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት፣ ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ሄደህ አምጣቸው’ ያልሁት እንደ ሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ክፉ ነገር አያገኝህም፤ አደጋም የለም፤ ውጣና ና። 22ነገር ግን ልጁን፣ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት ከአንተ ወዲያ ዐልፎ ነው’ ያልሁት እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንድትሄድ ፈቅዷልና ሂድ። 23አንተና እኔ ስለ ተነጋገርነው ነገር እነሆ፤ እግዚአብሔር በመካከላችን ለዘላለም ምስክር ነው።”
24ስለዚህም ዳዊት በዱር ተደበቀ፤ የወር መባቻ በዓል በተከበረበት ጊዜ፣ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ፤ 25ንጉሡ እንደ ወትሮው በግድግዳው#20፥25 የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ዮናታን ሲነሣ ይላል። አጠገብ ተቀመጠ፤ ዮናታን ከፊት ለፊቱ፣ አበኔር ደግሞ ከአጠገቡ ተቀመጡ፤ የዳዊት መቀመጫ ግን ባዶ ነበር። 26ሳኦልም፣ “ዳዊት በሥርዐቱ መሠረት እንዳይነጻ የሚያደርገው አንድ ነገር ገጥሞታል፤ በርግጥም አልነጻም” ብሎ ስላሰበ፣ በዚያ ቀን ምንም አልተናገረም። 27በማግስቱም፣ ወር በገባ በሁለተኛው ቀን የዳዊት መቀመጫ ባዶ ነበር፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ዮናታንን፣ “የእሴይ ልጅ ትናንትናም፣ ዛሬም ግብር ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
28ዮናታንም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄድ እፈቅድለት ዘንድ አጥብቆ ለመነኝ። 29እርሱም ‘ቤተ ሰባችን በከተማዪቱ ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያደርግ በዚያ እንድገኝ ወንድሜ አዞኛልና ልሂድ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ወንድሞቼን ለማየት እንድሄድ አሰናብተኝ’ አለኝ። በንጉሡ ግብር ላይ ሳይገኝ የቀረውም በዚህ ምክንያት ነው።”
30ሳኦል በዮናታን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አንተ የዚያች ጠማማና ዐመፀኛ ሴት ልጅ! ለአንተው ለራስህ ውርደት፣ ለወላጅ እናትህም ዕፍረት ከሚሆነው ከእሴይ ልጅ ጋራ መግጠምህን የማላውቅ መሰለህ? 31የእሴይ ልጅ በምድር ላይ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተም ሆንህ መንግሥትህ አትጸኑም። መሞት ስለሚገባው፣ ሰው ላክና አስመጣልኝ!”
32ዮናታንም፣ “ለምን ይገደላል? ጥፋቱስ ምንድን ነው?” ሲል አባቱን ጠየቀ። 33ሳኦልም ዮናታንን ለመግደል ጦሩን ወረወረበት። ስለዚህ ዮናታን፣ አባቱ ዳዊትን ለመግደል ቈርጦ መነሣቱን ዐወቀ።
34ዮናታንም በታላቅ ቍጣ ከግብሩ ላይ ተነሣ፤ አባቱም ዳዊትን ስላዋረደው ወሩ በገባ በሁለተኛው ቀን ምግብ አልበላም።
35በማግስቱም ጧት ዮናታን አንድ ትንሽ ልጅ አስከትሎ፣ ከዳዊት ጋራ ወደ ተቃጠረበት ቦታ ሄደ፤ 36ልጁንም፣ “ሩጥ! የምሰዳቸውን ፍላጻዎች ፈልጋቸው” አለው፤ ልጁም በሮጠ ጊዜ፣ ከርሱ አሳልፎ አንድ ፍላጻ ወረወረ። 37ልጁም የዮናታን ፍላጻ ባረፈበት ስፍራ እንደ ደረሰ፤ ዮናታን ጠራውና፣ “ፍላጻው ካንተ ወዲያ ዐልፎ የለምን?” አለው።
38እርሱም “ቶሎ በል! ፍጠን! አትቁም!” ሲል ጮኸበት፤ ልጁም ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው ተመለሰ። 39ከዮናታንና ከዳዊት በቀር ልጁ ስለዚህ ነገር የሚያውቀው አንዳች አልነበረም። 40ከዚያም ዮናታን የጦር መሣሪያውን ለልጁ ሰጥቶ፣ “ይዘህ ወደ ከተማ ተመለስ” አለው።
41ልጁ ከሄደ በኋላ፣ ዳዊት ከድንጋዩ በስተ ደቡብ ከተደበቀበት ቦታ ወጥቶ በዮናታን ፊት ሦስት ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደለት፤ ከዚያም ተሳሳሙ፤ ተላቀሱም፤ በይበልጥ ያለቀሰው ግን ዳዊት ነበር።
42ዮናታንም ዳዊትን፤ “ ‘በአንተና በእኔ፣ በዘሮችህና በዘሮቼ መካከል እግዚአብሔር ለዘላለም ምስክር ነው’ ተባብለን ወዳጅነታችን እንዲጸና በእግዚአብሔር ስም ስለ ተማማልን እንግዲህ በሰላም ሂድ” አለው። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ተመለሰ።

Currently Selected:

1 ሳሙኤል 20: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ