1 ሳሙኤል 21

21
ዳዊት ወደ ኖብ ሄደ
1ዳዊትም ካህኑ አቢሜሌክ ወዳለበት ወደ ኖብ ሄደ። አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና፣ “ምነው ብቻህን? ሰውስ ለምን ዐብሮህ የለም?” ሲል ጠየቀው።
2ዳዊት፣ ካህኑን አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ፣ ‘ስለ ላክሁህ ነገርና ስለ ሰጠሁህ መመሪያ ማንም ሰው ምንም ነገር አይወቅ’ ብሎ አዞኛል። ሰዎቼንም የት እንደምንገናኝ ነግሬያቸዋለሁ። 3ታዲያ አሁን በእጅህ ምን አለ? ዐምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።”
4ካህኑም ዳዊትን፣ “ሰው ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፤ ነገር ግን ሰዎቹ በቅርቡ ከሴት የተጠበቁ ከሆነ፣ የተቀደሰ እንጀራ በዚህ አለ” አለው።
5ዳዊትም “እንደተለመደው ሁሉ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ከእኛ ተጠብቀዋል፤ ባልተቀደሰ ተልእኮ ውስጥ እንኳ የሰዎቹ ዕቃዎች#21፥5 ወይም አካል የተቀደሱ ናቸው፤ ታዲያ ዛሬማ እንዴት!” ሲል ለካህኑ መለሰ። 6ስለዚህ ካህኑ የተቀደሰውን እንጀራ ለዳዊት ሰጠው፤ ከእግዚአብሔር ፊት ተነሥቶ በትኵስ እንጀራ ከተተካው ከገጸ ኅብስቱ በቀር በዚያ ሌላ እንጀራ አልነበረምና።
7በዚያችም ዕለት ከሳኦል አገልጋዮች አንዱና የእረኞቹ አለቃ የሆነው ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያው በእግዚአብሔር ፊት እንዲቈይ ተገዶ ነበር።
8ዳዊት አቢሜሌክን፣ “የንጉሡ ጕዳይ ስላስቸኰለኝ፣ ሰይፌንም ሆነ ሌላ የጦር መሣሪያ አላመጣሁም፤ እዚህ ካንተ ዘንድ ጦር ወይም ሰይፍ አይገኝምን?” ሲል ጠየቀው።
9ካህኑም፣ “በኤላ ሸለቆ አንተ የገደልኸው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ እዚህ አለ፤ ከኤፉዱ በስተኋላ በጨርቅ ተጠቅልሏል ከፈለግህ ውሰደው፤ ከርሱ በቀር ሌላ ሰይፍ እዚህ የለም” ብሎ መለሰለት።
ዳዊትም “እንደ እርሱ ያለ የለምና እርሱኑ ስጠኝ” አለው።
ዳዊት ወደ ጌት ሄደ
10በዚያች ዕለት ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ ወደ ጋት ንጉሥ ወደ አንኩስ ሄደ። 11የአንኩስ አገልጋዮችም፣ “የምድሪቱ ንጉሥ ዳዊት ይህ አይደለምን? ደግሞስ፣
“ ‘ሳኦል ሺሕ ገደለ፤
ዳዊት ግን ዐሥር ሺሕ ገደለ’
ብለው በጭፈራቸው የዘፈኑለትስ እርሱ አይደለምን?” አሉት።
12ዳዊት ነገሩን በልቡ አኖረ፤ የጋትን ንጉሥ አንኩስንም እጅግ ፈራው። 13ስለዚህ በፊታቸው አእምሮውን እንደ ሳተ ሰው ሆነ፤ በያዙትም ጊዜ የከተማዪቱን ቅጥሮች እየቦጫጨረ፣ ልጋጉንም በጢሙ ላይ እያዝረበረበ እንደ እብድ ሆነ።
14አንኩስም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሰውየውን እስኪ ተመልከቱት፤ እብድ እኮ ነው! ታዲያ ወደ እኔ ያመጣችሁት ለምንድን ነው? 15በፊቴ እንዲህ ይሆን ዘንድ ይህን ሰው እዚህ ያመጣችሁት እብድ ዐጥቼ ነውን? እንዲህ ያለውስ ሰው ወደ ቤቴ መግባት ይገባዋልን?”

Currently Selected:

1 ሳሙኤል 21: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ