1 ሳሙኤል 22
22
ዳዊት በዓዶላምና በምጽጳ
1ዳዊት ከጌት ወደ ዓዶላም ዋሻ ሸሸ፤ ወንድሞቹና የአባቱ ቤተ ሰቦች ይህን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱ ወዳለበት ወደዚያው ወረዱ። 2የተጨነቁ፣ ዕዳ ያለባቸውና የተከፉ አራት መቶ ያህል ሰዎች፣ ወደ እርሱ ተሰባሰቡ፤ መሪያቸውም ሆነ።
3ዳዊት ከዚያ ተነሥቶ፣ በሞዓብ ምድር ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ ለሞዓብ ንጉሥ፣ “እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ፣ አባቴና እናቴ መጥተው ካንተ ዘንድ እንዲቀመጡ ፈቃድህ ነውን?” አለው። 4እርሱም በሞዓብ ንጉሥ ዘንድ አስቀመጣቸው፤ ዳዊት በዐምባ ውስጥ እስከ ቈየበትም ጊዜ ድረስ ከንጉሡ ዘንድ ተቀመጡ።
5ይሁን እንጂ ነቢዩ ጋድ ዳዊትን፣ “በዐምባው ውስጥ አትቈይ፤ ሂድና ወደ ይሁዳ ምድር ግባ” አለው። ስለዚህ ዳዊት ተነሥቶ ወደ ሔሬት ጫካ ገባ።
ሳኦል የኖብን ካህናት መግደሉ
6ሳኦልም፣ ዳዊትና ከርሱ ጋራ የነበሩ ሰዎች መገኘታቸውን በሰማ ጊዜ፣ በጊብዓ ኰረብታ ላይ በአጣጥ ዛፍ ሥር፣ ጦሩን በእጁ ይዞ ተቀምጦ ነበር፤ ሹማምቱም ሁሉ በዙሪያው ቆመው ነበር። 7ሳኦልም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የብንያም ሰዎች ስሙ! በውኑ የእሴይ ልጅ ዕርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ ሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋችኋልን? 8በእኔ ላይ የዶለታችሁት ለዚህ ነውን? ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋራ ቃል ኪዳን ሲያደርግ ማንም አልነገረኝም፤ ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ልጄ አገልጋዬን በእኔ ላይ እንዲያደባብኝ ማነሣሣቱን ከእናንተ ስለ እኔ ተቈርቍሮ የነገረኝ ማንም የለም።”
9ነገር ግን እዚያ ከነበሩት የሳኦል ሹማምት ጋራ ቆሞ የነበረው ኤዶማዊው ዶይቅ እንዲህ አለ፣ “የእሴይ ልጅ በኖብ ወዳለው ወደ አኪጦብ ልጅ ወደ አቢሜሌክ ሲመጣ አይቻለሁ። 10አቢሜሌክም እግዚአብሔርን ጠየቀለት፤ እንዲሁም ስንቅና የፍልስጥኤማዊውን የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው።”
11ከዚያም ንጉሡ፣ የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቢሜሌክን፣ በኖብ ካህናት የነበሩትን የአባቱን ቤተ ሰብ በሙሉ ልኮ አስጠራቸው፤ ሁሉም ወደ ንጉሡ መጡ። 12ሳኦልም፤ “የአኪጦብ ልጅ ሆይ፤ እንግዲህ ስማ” አለው።
አቢሜሌክም፣ “ዕሺ ጌታዬ” ብሎ መለሰ።
13ሳኦልም፤ “ዛሬ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ በእኔ ላይ እንዲያምፅብኝና እንዲያደባብኝ፣ እንጀራና ሰይፍ በመስጠት፣ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ በመጠየቅ ከእሴይ ልጅ ጋራ ለምን ዶለታችሁብኝ?” አለው።
14አቢሜሌክም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የንጉሥ ዐማች፣ የክብር ዘቦችህ አዛዥና በቤተ ሰብህ ዘንድ እጅግ የተከበረው ዳዊትን የመሰለ ታማኝ ከአገልጋዮችህ ሁሉ ማን አለ? 15ስለ እርሱ እግዚአብሔርን ስጠይቅስ ያ ቀን የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበርን? ፈጽሞ አልነበረም፤ ይህን ጕዳይ በተመለከተ አገልጋይህ የሚያውቀው ምንም ነገር ስለሌለ ንጉሥ እኔን አገልጋዩን ወይም ከአባቴ ቤተ ሰብ ማንንም ጥፋተኛ አያድርግ።”
16ንጉሡ ግን፣ “አቢሜሌክ ሆይ፤ አንተም የአባትህም ቤተ ሰብ በሙሉ በርግጥ ትሞታላችሁ” አለው።
17ከዚያም ንጉሡ በአጠገቡ የቆሙትን ዘቦች፣ “እነዚህም የእግዚአብሔር ካህናት ከዳዊት ጋራ ስላበሩ፣ ዳዊት መኰብለሉንም እያወቁ ስላልነገሩኝ ዙሩና ግደሏቸው” ሲል አዘዛቸው።
የንጉሡ ሹማምት ግን እጃቸውን አንሥተው የእግዚአብሔርን ካህናት ለመምታት ፈቃደኞች አልሆኑም።
18ንጉሡም ዶይቅን፣ “እንግዲያውስ አንተው ዙርና ካህናቱን ግደላቸው” ብሎ አዘዘው። ኤዶማዊው ዶይቅም ዞረና ገደላቸው። በዚያች ዕለት ሰማንያ ዐምስት የበፍታ ኤፉድ የለበሱ ካህናትን ገደለ። 19የካህናቱንም ከተማ ኖብን በሰይፍ መታት፣ በዚያ የሚኖሩትንም ወንዶችንና ሴቶችን፣ ልጆችንና ጡት የሚጠቡ ሕፃናትን፣ እንዲሁም በሬዎችንና አህያዎችን፣ በጎችንም ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጃቸው።
20የአኪጦብ ልጅ፣ የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ግን አምልጦ ዳዊት ወዳለበት ሸሸ። 21አብያታርም ሳኦል የእግዚአብሔርን ካህናት እንደ ገደላቸው ለዳዊት ነገረው። 22ዳዊትም አብያታርን እንዲህ አለው፤ “ያን ዕለት ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያ ስለ ነበር፣ ነገሩን በትክክል ለሳኦል እንደሚናገር ዐውቄአለሁ፤ ለመላው የአባትህ ቤተ ሰብ ዕልቂት ተጠያቂው እኔ ነኝ። 23አሁንም ከእኔ ጋራ ቈይ፤ አትፍራ፤ የአንተን ሕይወት የሚፈልግ የእኔን ሕይወት የሚፈልግ ነውና። ዐብረኸኝ በሰላም ትኖራለህ።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.