የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 10

10
ቆርኔሌዎስ ጴጥሮስን አስጠራ
1በቂሳርያ፣ “የኢጣሊያ ክፍለ ጦር” በሚባለው ሰራዊት ውስጥ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። 2እርሱም ከመላው ቤተ ሰቡ ጋራ በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ለሰዎች እጅግ ምጽዋት የሚሰጥ፣ አዘውትሮ ወደ እግዚአብሔር የሚጸልይ ነበር። 3አንድ ቀን፣ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” ሲለው በግልጽ አየ።
4ቆርኔሌዎስም በድንጋጤ ትኵር ብሎ እያየው፣ “ጌታ ሆይ፤ ምንድን ነው?” አለው።
መልአኩም እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህና ምጽዋትህ ለመታሰቢያነት ወደ እግዚአብሔር ፊት ዐርጎልሃል። 5አሁንም ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤ 6እርሱ አሁን በባሕር አጠገብ በሚገኘው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጧል።”
7ቆርኔሌዎስም፣ ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት ከሄደ በኋላ፣ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ነገር የተጋና ለርሱ ታማኝ የሆነውን አንዱን ወታደር አስጠራ፤ 8የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው።
ጴጥሮስ ያየው ራእይ
10፥9-32 ተጓ ምብ – ሐሥ 11፥5-14
9የተላኩትም ሰዎች በማግስቱም ወደ ከተማዪቱ እንደ ተቃረቡ፣ ጴጥሮስ እኩለ ቀን ገደማ ሲሆን፣ ለመጸለይ ወደ ሰገነት ወጣ። 10በዚያ ጊዜም ስለ ተራበ የሚበላ ነገር ፈለገ፤ ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም አሸለበውና በተመስጦ ውስጥ ሆነ፤ 11ሰማይም ተከፍቶ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራት ማእዘን ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ። 12በጨርቁም ላይ አራት እግር ያላቸው የተለያዩ እንስሳት፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትና በአየር የሚበርሩ አዕዋፍ ነበሩበት። 13በዚህ ጊዜ፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣ፤ እነዚህን ዐርደህ ብላ” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።
14ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! ይህማ አይሆንም፤ እኔ ያልተቀደሰ ወይም ርኩስ ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅምና” አለ።
15ያም ድምፅ እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቍጠረው” አለው።
16ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ጨርቁም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ።
17ጴጥሮስም ስላየው ራእይ ትርጕም እጅግ ተጨንቆ በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት ፈልገው ካገኙ በኋላ መጥተው በሩ ላይ ቆሙ፤ 18ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን እዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ።
19ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ መንፈስ እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ሦስት#10፥19 አንድ የጥንት ቅጅ ሁለት ይላል፤ ሌሎች የጥንት ቅጆች ይህ ቍጥር የላቸውም። ሰዎች ይፈልጉሃል፤ 20ስለዚህ ተነሥተህ ውረድ፤ የላክኋቸውም እኔ ስለ ሆንሁ፣ ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋራ ሂድ።”
21ጴጥሮስም ወርዶ፣ “እነሆ፤ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ጕዳይ ምንድን ነው?” አላቸው።
22ሰዎቹ፣ “የመጣነው ቆርኔሌዎስ ከተባለው መቶ አለቃ ዘንድ ነው፤ እርሱም ጻድቅና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተከበረ ሰው ነው። አንተን ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ነግሮታል” አሉት። 23ጴጥሮስም ሰዎቹን ሊያስተናግዳቸው ወደ ቤት አስገባቸው።
ጴጥሮስ በቆርኔሌዎስ ቤት
ጴጥሮስም በማግስቱም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋራ ሄደ፤ ከኢዮጴ የመጡ አንዳንድ ወንድሞችም ዐብረውት ሄዱ፤ 24በሚቀጥለው ቀን ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ ይጠብቃቸው ነበር። 25ጴጥሮስም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ እግሩም ላይ ወድቆ ሰገደለት። 26ጴጥሮስ ግን፣ “እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝና ተነሥ!” ብሎ አስነሣው።
27ጴጥሮስም እያነጋገረው ዐብሮት ሲገባ፣ ብዙ ሰው ተሰብስቦ አገኘ፤ 28እንዲህም አላቸው፤ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ወገን ጋራ እንዲተባበር ወይም እንዲቀራረብ ሕጋችን እንደማይፈቅድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ ማንንም ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳይቶኛል። 29ስለዚህም በተጠራሁ ጊዜ፣ እነሆ ሳላመነታ መጣሁ፤ እንግዲህ፣ ለምን እንደ ጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።”
30ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፤ “ከአራት ቀን በፊት በዚህ ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ ሆኜ እጸልይ ነበር፤ ድንገትም ብሩህ ልብስ የለበሰ ሰው መጥቶ በፊቴ ቆመና 31እንዲህ አለኝ፤ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ፤ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ምጽዋትህም ለመታሰቢያነት በእግዚአብሔር ፊት ደርሷል። 32ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤ እርሱም በባሕሩ አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፏል።’ 33እኔም ወዲያው ላክሁብህ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ እኛ ሁላችን ጌታ ያዘዘህን ስትነግረን ለመስማት በእግዚአብሔር ፊት አለን።”
34ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእውነት ተረድቻለሁ፤ 35ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል። 36እግዚአብሔር፣ የሁሉ ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እስራኤል ሕዝብ የላከውም የሰላም የምሥራች መልእክት ይኸው ነው። 37ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በመላው ይሁዳ የሆነውን ታውቃላችሁ፤ 38እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ።
39“እርሱ በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ላደረገው ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ ደግሞም ሰዎች እርሱን በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። 40እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን አስነሣው፤ እንዲታይም አደረገው፤ 41የታየውም ለሁሉ ሰው ሳይሆን፣ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ዐብረነው ለበላንና ለጠጣን፣ እግዚአብሔርም አስቀድሞ ለመረጠን ለእኛ ለምስክሮቹ ነው። 42ለሕዝቡ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ እግዚአብሔር የሾመው እርሱ መሆኑን እንድንመሰክር እርሱ ራሱ አዘዘን፤ 43በርሱም የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአትን ስርየት እንደሚቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።”
44ጴጥሮስ ይህን እየተናገረ ሳለ፣ ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። 45ከጴጥሮስ ጋራ የመጡት፣ ከተገረዙት ወገን የሆኑት አማኞች፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛብም ላይ ደግሞ መፍሰሱን ሲያዩ ተገረሙ። 46ይኸውም በልሳን#10፥46 ወይም በሌላ ቋንቋዎች ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ስለ ሰሟቸው ነው።
በዚያ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ አለ፤ 47“እነዚህ ሰዎች እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ስለ ተቀበሉ፣ እንግዲህ በውሃ እንዳይጠመቁ የሚከለክላቸው ማን ነው?” 48ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ፣ ጴጥሮስ ጥቂት ቀን ከእነርሱ ጋራ እንዲቀመጥ ለመኑት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ