የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 9

9
የሳውል ማመን
9፥1-19 ተጓ ምብ – ሐሥ 22፥3-1626፥9-18
1ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል አሁንም እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፤ 2የጌታን መንገድ የሚከተሉትን ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን በዚያ ካገኘ አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ እንዲችል፣ በደማስቆ ለነበሩት ምኵራቦች ደብዳቤ እንዲሰጠው ሊቀ ካህናቱን ለመነው። 3ደማስቆ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው፣ ብርሃን ከሰማይ ድንገት በዙሪያው አንጸባረቀበት፤ 4እርሱም በመሬት ላይ ወደቀ፤ በዚያ ጊዜም “ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ።
5ሳውልም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?” አለው።
እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔማ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። 6ነገር ግን ተነሣና ወደ ከተማዪቱ ግባ፤ ማድረግ የሚገባህም ይነገርሃል።”
7ከሳውል ጋራ ይጓዙ የነበሩትም ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንንም ባላዩ ጊዜ፣ አፋቸውን ይዘው ቆሙ። 8ሳውልም ከመሬት ላይ ተነሥቶ ዐይኑን ሲገልጥ ምንም ማየት አልቻለም፤ ስለዚህ ሰዎቹ እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አስገቡት። 9ሦስት ቀንም ታወረ፤ እህል ውሃም አልቀመሰም።
10በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ፣ “ሐናንያ!” ብሎ ጠራው።
እርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆኝ” አለ።
11ጌታም እንዲህ አለው፤ “ተነሣና ‘ቀጥተኛ ጐዳና’ በተባለው መንገድ ይሁዳ ወደ ተባለ ሰው ቤት ሂድ፤ እዚያም ሳውል የሚባል አንድ የጠርሴስ ሰው እየጸለየ ነውና ፈልገው፤ 12እርሱም ሐናንያ የሚባል ሰው እርሱ ወዳለበት መጥቶ እጁን እንደሚጭንበትና ዐይኑ እንደሚበራለት በራእይ አይቷል።”
13ሐናንያም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ይህ ሰው እኮ በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳንህ ላይ ምን ያህል ጕዳት እንዳደረሰ ከብዙ ሰው ሰምቻለሁ፤ 14ወደዚህም የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብሎ ነው።”
15ጌታም እንዲህ አለው፤ “ሂድ! ይህ ሰው በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው፤ 16እኔም ስለ ስሜ ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት አሳየዋለሁ።”
17ሐናንያ ሄዶ፣ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ በሳውልም ላይ እጁን ጭኖ፣ “ወንድሜ ሳውል ሆይ፤ ወደዚህ ስትመጣ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ፣ ዐይንህ እንዲበራና በመንፈስ ቅዱስም እንድትሞላ እኔን ልኮኛል” አለው። 18ወዲያውም ከሳውል ዐይን ላይ ቅርፊት የመሰለ ነገር ወደቀ፤ እንደ ገና ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ 19ምግብም በልቶ በረታ።
ሳውል በደማስቆና በኢየሩሳሌም
ሳውል በደማስቆ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ጋራ አያሌ ቀን ተቀመጠ። 20ወዲያውም፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በየምኵራቦቹ መስበክ ጀመረ። 21የሰሙትም ሁሉ በመገረም፣ ይህ ሰው “በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረ አይደለምን? ደግሞም ወደዚህ የመጣው እነርሱን አስሮ ወደ ካህናት አለቆች ሊወስዳቸው አልነበረምን?” አሉ። 22ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ ለሚኖሩትም አይሁድ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ#9፥22 ወይም መሲሕ መሆኑን ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር።
23ከብዙ ቀንም በኋላ፣ አይሁድ ሳውልን ለመግደል አሤሩ፤ 24ሳውል ግን ዕቅዳቸውን ዐውቆ ነበር፤ እነርሱም ሊገድሉት የከተማዋን በር ቀንና ሌሊት ይጠብቁ ነበር፤ 25የርሱ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት በከተማዪቱ ቅጥር ቀዳዳ አሹልከው በቅርጫት አወረዱት።
26ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርት ጋራ ለመቀላቀል ሞከረ፤ እነርሱ ግን በርግጥ ደቀ መዝሙር መሆኑን ስላላመኑ ሁሉም ፈሩት። 27ይሁን እንጂ በርናባስ ወስዶ ወደ ሐዋርያት አመጣው፤ ሳውልም በጕዞው ላይ ሳለ ጌታን እንዴት እንዳየው፣ ጌታም እንዴት እንደ ተናገረው እንዲሁም በደማስቆ በኢየሱስ ስም እንዴት በድፍረት እንደ ሰበከ ነገራቸው። 28ስለዚህ ሳውል ዐብሯቸው ተቀመጠ፤ በኢየሩሳሌምም በመዘዋወር በጌታ ስም በድፍረት ይናገር ነበር። 29ከግሪክ አገር ከመጡት አይሁድ ጋራ እየተነጋገረ ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ጥረት ያደርጉ ነበር። 30ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ፣ ወደ ቂሳርያ አውርደው ወደ ጠርሴስ ሰደዱት።
31በዚህ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሰላም መኖር ጀመረች፤ ተጠናከረችም። ደግሞም ጌታን በመፍራት እየተመላለሰችና በመንፈስ ቅዱስ እየተጽናናች በቍጥር እየበዛች ሄደች።
ኤንያና ዶርቃ
32ጴጥሮስም ከአገር ወደ አገር በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ በልዳ የሚኖሩትን ቅዱሳን ለመጐብኘት ወረደ። 33በዚያም ኤንያ የተባለ፣ ስምንት ዓመት የዐልጋ ቍራኛ የነበረ አንድ ሽባ ሰው አገኘ። 34ጴጥሮስም፣ “ኤንያ ሆይ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣና መኝታህን አንጥፍ” አለው። ኤንያም ወዲያውኑ ብድግ አለ። 35በልዳና በሰሮና የሚኖሩትም ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ተመለሱ።
36በኢዮጴ ጣቢታ የተባለች አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ የስሟም ትርጓሜ ዶርቃ#9፥36 ጣቢታ በአራማይክ ሲሆን፣ ዶርቃ ደግሞ በግሪክ ነው፤ ትርጕሙም ፌቆ (ሚዳቋ) ማለት ነው። ማለት ነው። እርሷም ዘወትር በትጋት በጎ ነገር እያደረገችና ድኾችን እየረዳች ትኖር ነበር። 37በዚያ ጊዜም ታምማ ሞተች፤ ሰዎችም አስከሬኗን ዐጥበው በሰገነት ላይ ባለው ክፍል አስቀመጡት። 38ልዳ ለኢዮጴ ቅርብ ስለ ነበረች፣ ደቀ መዛሙርትም ጴጥሮስ በልዳ መሆኑን በሰሙ ጊዜ ሁለት ሰዎች ልከው፣ “እባክህ ፈጥነህ ወደ እኛ ና!” ሲሉ ለመኑት።
39ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋራ ሄደ፤ እዚያ በደረሰ ጊዜም ሰገነት ላይ ወዳለው ክፍል አወጡት። መበለቶቹም ሁሉ ዶርቃ ከእነርሱ ጋራ በነበረችበት ጊዜ ያደረገቻቸውን ቀሚሶችና ልብሶች እያሳዩት ዙሪያውን ከብበው ያለቅሱ ነበር።
40ጴጥሮስም ሁሉንም ከክፍሉ አስወጥቶ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ፣ “ጣቢታ፤ ተነሺ” አለ። እርሷም ዐይኗን ገለጠች፤ ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ቀና ብላ ተቀመጠች፤ 41እርሱም እጇን ይዞ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶቹንም ጠርቶ ከነሕይወቷ አስረከባቸው። 42ይህም ነገር በመላው ኢዮጴ ታወቀ፤ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ። 43ጴጥሮስም ስምዖን ከተባለ ከአንድ ቍርበት ፋቂ ጋራ በኢዮጴ ብዙ ቀን ተቀመጠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ