እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በርሱ ኑሩ፤ በርሱ ተተክላችሁና ታንጻችሁ እንደ ተማራችሁት በእምነት ጸንታችሁ፣ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ። በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ወግና በዚህ ዓለም መሠረታዊ መንፈሳዊ ኀይሎች ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ። የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በርሱ ይኖራልና፤ እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል። በርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤ በጥምቀትም ከርሱ ጋራ ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከርሱ ጋራ ደግሞ ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁ፣ እግዚአብሔር ግን ከክርስቶስ ጋራ ሕያዋን አደረጋችሁ፤ በደላችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤ ሲቃወመንና ሲፃረረን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ከነሕግጋቱ በመደምሰስ፣ በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው። የገዦችና የባለሥልጣናትንም ማዕርግ በመግፈፍ በመስቀሉ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ። እንግዲህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ ወር መባቻንና ሰንበትን በማክበር ነገር ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ላሉ ነገሮች ጥላ ናቸውና፤ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ዐጕል ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ የሚወድድ ማንም ሰው እንዳያደናቅፋችሁ ተጠንቀቁ። እንደዚህ ያለ ሰው ስላየው ራእይ ከመጠን በላይ ራሱን እየካበ በሥጋዊ አእምሮው ከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይታበያል፤ ይህ ሰው፣ አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ እየተጋጠመ ምግብንም እየተቀበለ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ከሚያድግበት ራስ ከሆነው ጋራ ግንኙነት የለውም። ለዚህ ዓለም መርሕ ከክርስቶስ ጋራ ከሞታችሁ፣ ታዲያ በዚህ ዓለም እንደሚኖር ለምን ትገዙላቸዋላችሁ? “አትያዝ! አትቅመስ! አትንካ!” እንደሚሉት ዐይነት፣ እነዚህ ሁሉ በሰው ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠፊ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጕል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንጻር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም።
ቈላስይስ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ቈላስይስ 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ቈላስይስ 2:6-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች