ቈላስይስ 2:6-23
ቈላስይስ 2:6-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ተቀበላችሁት፥ በእርሱ ተመላለሱ። በእርሱ ተመሥርታችሁ ታነጹ፤ በምስጋናው ትበዙ ዘንድ፥ በተማራችሁት ሃይማኖት ጽኑ። ለዚህ ዓለም ስሕተት፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ፥ በሰው ሠራሽ ሥርዐት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሉአችሁ፥ ተጠንቀቁ። በእርሱ ፍጹም መለኮቱ በሥጋ ተገልጦ ይኖራልና። እናንተም በእርሱ ፍጹማን ሁኑ፤ እርሱ ለአለቅነት ሁሉና ለሥልጣን ሁሉ ራስ ነውና። የኀጢአትን ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል። እናንተም በኀጢአታችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁና፥ ከእርሱ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር አላችሁ። ከባላጋራችን የተነሣ በትእዛዝ የተጻፈውን የዕዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን፤ ከመካከላችንም አራቀው፤ በመስቀሉም ቸነከረው። አለቆችንና ገዢዎችን በመግፈፉ በግልጥ አሳያቸው፤ ራቁቱን በመሆኑም አሳፈራቸው። እንግዲህ በመብልም ቢሆን፥ በመጠጥም ቢሆን፥ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን፥ በመባቻም ቢሆን፥ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ። ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ፥ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር። ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት፥ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት፥ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት፥ በሚሞላበትም በራስ አይጸናም። ከዚህ ዓለም ኑሮ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ እንደገና በዓለም እንደሚኖሩ ሰዎች እንዴት ትሠራላችሁ? እንዴትስ ይህን አትዳስስ፥ ይህን አትንካ፥ ይህንም አትቅመስ ይሉአችኋል? ይህ ሁሉ እንደ ሰው ትእዛዝና ትምህርት ለጥፋት ነውና። ይህም ስለ ልብ ትሕትናና እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት፥ ለሥጋ ስለ አለማዘን ጥበብን ይመስላል፤ ነገር ግን ከሥጋ በላይ ነው እንጂ ምንም ክብር የለውም።
ቈላስይስ 2:6-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በርሱ ኑሩ፤ በርሱ ተተክላችሁና ታንጻችሁ እንደ ተማራችሁት በእምነት ጸንታችሁ፣ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ። በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ወግና በዚህ ዓለም መሠረታዊ መንፈሳዊ ኀይሎች ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ። የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በርሱ ይኖራልና፤ እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል። በርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤ በጥምቀትም ከርሱ ጋራ ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከርሱ ጋራ ደግሞ ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁ፣ እግዚአብሔር ግን ከክርስቶስ ጋራ ሕያዋን አደረጋችሁ፤ በደላችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤ ሲቃወመንና ሲፃረረን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ከነሕግጋቱ በመደምሰስ፣ በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው። የገዦችና የባለሥልጣናትንም ማዕርግ በመግፈፍ በመስቀሉ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ። እንግዲህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ ወር መባቻንና ሰንበትን በማክበር ነገር ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ላሉ ነገሮች ጥላ ናቸውና፤ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ዐጕል ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ የሚወድድ ማንም ሰው እንዳያደናቅፋችሁ ተጠንቀቁ። እንደዚህ ያለ ሰው ስላየው ራእይ ከመጠን በላይ ራሱን እየካበ በሥጋዊ አእምሮው ከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይታበያል፤ ይህ ሰው፣ አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ እየተጋጠመ ምግብንም እየተቀበለ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ከሚያድግበት ራስ ከሆነው ጋራ ግንኙነት የለውም። ለዚህ ዓለም መርሕ ከክርስቶስ ጋራ ከሞታችሁ፣ ታዲያ በዚህ ዓለም እንደሚኖር ለምን ትገዙላቸዋላችሁ? “አትያዝ! አትቅመስ! አትንካ!” እንደሚሉት ዐይነት፣ እነዚህ ሁሉ በሰው ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠፊ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጕል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንጻር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም።
ቈላስይስ 2:6-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፤ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፤ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል። ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት፦ አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም።
ቈላስይስ 2:6-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደተቀበላችሁት በእርሱ ኑሩ፤ በእርሱ ተመሥርታችሁና ታንጻችሁ፥ በተማራችሁት መሠረት፥ በእምነታችሁ ጸንታችሁ ኑሩ፤ ሞልቶ የሚተርፍ ምስጋናም አቅርቡ። በክርስቶስ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በሰው ሠራሽ ወግና በዓለማዊ ተራ ሥርዓት ላይ በተመሠረተ በፍልስፍናና በከንቱ ሽንገላ ማንም እንዳያጠምዳችሁ ተጠንቀቁ። የአምላክነት ፍጹም ሙላት በአካል ተገልጦ የሚኖረው በክርስቶስ ነው። እናንተም ሙሉ ሕይወትን ያገኛችሁት በፍጥረቱ ሁሉ ላይ የግዛትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ነው። በእርሱም በማመናችሁ ተገርዛችኋል፤ ይህም መገረዛችሁ ኃጢአተኛውን የሥጋ ባሕርይ ለማስወገድ በክርስቶስ የተደረገ ነው እንጂ በሰው እጅ የተደረገ አይደለም። በተጠመቃችሁ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ተቀበራችሁ፤ ከእርሱም ጋር ከሞት ተነሥታችኋል፤ ከሞት የተነሣችሁትም ክርስቶስን ከሞት ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመናችሁ ነው። ኃጢአት በመሥራታችሁና የኃጢአተኛው ሥጋችሁ በክርስቶስ በማመን ባለመገረዙ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አድርጓችኋል፤ ኃጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር ብሎላችኋል። እርሱ ያንን ይከሰንና ይቃወመን የነበረውን በሕግ ያለውን የዕዳ ጽሑፍ ደመሰሰው፤ በመስቀል ላይ ቸንክሮም ከእኛ አስወገደው። ኀይሎችንና ባለሥልጣኖችን በመስቀሉ ድል ነሥቶ ትጥቃቸውን ካስፈታ በኋላ ምርኮኞች ሆነው በይፋ እንዲታዩ አደረጋቸው። እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ፥ በዓላትን ወይም የወር መባቻን፥ ወይም ሰንበትን በማክበር ምክንያት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሁሉ ወደፊት ይመጡ ለነበሩት ነገሮች እንደ ጥላ ናቸው፤ እውነቱ የሚገኘው ግን በክርስቶስ ነው። በአጉል ትሕትናና መላእክትን በማምለክ የሚመካ ማንም ሰው ያለ ዋጋ እንዳያስቀራችሁ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ዐይነቱ ሰው ስለሚያየው ራእይ እየተመጻደቀ ከንቱና ሥጋዊ በሆነ አስተሳሰብ ይታበያል። እንዲህ ያለ ሰው ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ አካልን በሙሉ በመገጣጠሚያና በጅማት አያይዞ የሚመግበው ራስ ነው። እግዚአብሔር ለአካል ሙሉ ዕድገት የሚሰጠውም በዚህ ዐይነት ነው። ከክርስቶስ ጋር ሞታችሁ ከዚህ ዓለም መሠረታዊ ሥርዓቶች ፈጽማችሁ የተለያችሁ ከሆናችሁ ታዲያ፥ አሁን ከዓለም እንዳልተለያችሁ ዐይነት ሆናችሁ ስለምን እንደዚህ ላሉት ትእዛዞች ትገዛላችሁ፤ ትእዛዞቹም “አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ” የሚሉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ በሰው ሠራሽ ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ ሥራ ላይ ከዋሉ በኋላ ለመጥፋት የተወሰኑ ናቸው። እነዚህ ትእዛዞች ከገዛ ፈቃድ በመነጨ አምልኮና በአጉል ትሕትና፥ ሰውነትንም በማጐሳቈል ላይ ስለሚያተኲሩ ጥበብ ያላቸው ይመስሉ ይሆናል፤ ነገር ግን ሥጋዊ ስሜትን በመቈጣጠር ረገድ ዋጋቢሶች ናቸው።
ቈላስይስ 2:6-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ አብዝታችሁ ምስጋናን በማቅረብ እንደ ተማራችሁት ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፤ በእምነትም ጽኑ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ መሠረታዊው የዓለም ረቂቅ መንፈስ በፍልስፍናና በከንቱ መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠንቀቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል ተገልጦ ይኖራልና፤ የአለቅነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። በክርስቶስ መገረዝ የሥጋዊውን አካል በመግፈፍ በሰው እጅ ባልተከናወነ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሞታችሁ የነበራችሁትን በደላችንን ሁሉ ይቅር ባለን ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ እርሱም ይፃረረንና ይቃወመን የነበረውን በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ በመስቀልም ላይ ቸንክሮ ከእኛ አስወገደው፤ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ በመስቀሉ ድል በመንሣት እነርሱን በይፋ አጋለጣቸው። እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ወደ ፊት ለሚመጡት ነገሮች እንደ ጥላ ናቸውና፤ እውነቱ የሚገኘው ግን በክርስቶስ ነው። ራስን ማዋረድና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባየውም ራእይ ላይ በጽኑ እየተመረኮዘ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ የሚያድገውን አካል ሁሉ የሚንከባከበውን በመገጣጠምያዎቹና በጅማቶቹ አብሮ የሚያስተሳስረውን ራስ በጽኑ ሳይዝ ማንም አያውግዛችሁ። ከመሠረታዊው የዓለም ረቂቅ መንፈስ ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ ከዓለም እንዳልተለያችሁ ዓይነት ኑሮ ለምን ትኖራላችሁ? ለምንስ እንደነዚህ ላሉት ትእዛዞች ትገዛላችሁ? እነርሱም፦ “አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ” የሚሉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ትእዛዛት በጥቅም ላይ በመዋላቸው የሚጠፉትን ነገሮች የሚጠቁሙ ናቸው፤ እንዲያው በቀላሉ የሰው ትእዛዛትና አስተምሮ ናቸው። እነዚህም በገዛ ፈቃድ የሚደረግ አምልኮንና ራስን ማዋረድ ሥጋንም የመጨቆን ጥበብ ያላቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅሙም።