ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደተቀበላችሁት በእርሱ ኑሩ፤ በእርሱ ተመሥርታችሁና ታንጻችሁ፥ በተማራችሁት መሠረት፥ በእምነታችሁ ጸንታችሁ ኑሩ፤ ሞልቶ የሚተርፍ ምስጋናም አቅርቡ። በክርስቶስ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በሰው ሠራሽ ወግና በዓለማዊ ተራ ሥርዓት ላይ በተመሠረተ በፍልስፍናና በከንቱ ሽንገላ ማንም እንዳያጠምዳችሁ ተጠንቀቁ። የአምላክነት ፍጹም ሙላት በአካል ተገልጦ የሚኖረው በክርስቶስ ነው። እናንተም ሙሉ ሕይወትን ያገኛችሁት በፍጥረቱ ሁሉ ላይ የግዛትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ነው። በእርሱም በማመናችሁ ተገርዛችኋል፤ ይህም መገረዛችሁ ኃጢአተኛውን የሥጋ ባሕርይ ለማስወገድ በክርስቶስ የተደረገ ነው እንጂ በሰው እጅ የተደረገ አይደለም። በተጠመቃችሁ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ተቀበራችሁ፤ ከእርሱም ጋር ከሞት ተነሥታችኋል፤ ከሞት የተነሣችሁትም ክርስቶስን ከሞት ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመናችሁ ነው። ኃጢአት በመሥራታችሁና የኃጢአተኛው ሥጋችሁ በክርስቶስ በማመን ባለመገረዙ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አድርጓችኋል፤ ኃጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር ብሎላችኋል። እርሱ ያንን ይከሰንና ይቃወመን የነበረውን በሕግ ያለውን የዕዳ ጽሑፍ ደመሰሰው፤ በመስቀል ላይ ቸንክሮም ከእኛ አስወገደው። ኀይሎችንና ባለሥልጣኖችን በመስቀሉ ድል ነሥቶ ትጥቃቸውን ካስፈታ በኋላ ምርኮኞች ሆነው በይፋ እንዲታዩ አደረጋቸው። እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ፥ በዓላትን ወይም የወር መባቻን፥ ወይም ሰንበትን በማክበር ምክንያት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሁሉ ወደፊት ይመጡ ለነበሩት ነገሮች እንደ ጥላ ናቸው፤ እውነቱ የሚገኘው ግን በክርስቶስ ነው። በአጉል ትሕትናና መላእክትን በማምለክ የሚመካ ማንም ሰው ያለ ዋጋ እንዳያስቀራችሁ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ዐይነቱ ሰው ስለሚያየው ራእይ እየተመጻደቀ ከንቱና ሥጋዊ በሆነ አስተሳሰብ ይታበያል። እንዲህ ያለ ሰው ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ አካልን በሙሉ በመገጣጠሚያና በጅማት አያይዞ የሚመግበው ራስ ነው። እግዚአብሔር ለአካል ሙሉ ዕድገት የሚሰጠውም በዚህ ዐይነት ነው። ከክርስቶስ ጋር ሞታችሁ ከዚህ ዓለም መሠረታዊ ሥርዓቶች ፈጽማችሁ የተለያችሁ ከሆናችሁ ታዲያ፥ አሁን ከዓለም እንዳልተለያችሁ ዐይነት ሆናችሁ ስለምን እንደዚህ ላሉት ትእዛዞች ትገዛላችሁ፤ ትእዛዞቹም “አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ” የሚሉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ በሰው ሠራሽ ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ ሥራ ላይ ከዋሉ በኋላ ለመጥፋት የተወሰኑ ናቸው። እነዚህ ትእዛዞች ከገዛ ፈቃድ በመነጨ አምልኮና በአጉል ትሕትና፥ ሰውነትንም በማጐሳቈል ላይ ስለሚያተኲሩ ጥበብ ያላቸው ይመስሉ ይሆናል፤ ነገር ግን ሥጋዊ ስሜትን በመቈጣጠር ረገድ ዋጋቢሶች ናቸው።
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2:6-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች