ወደ ቈላስይስ ሰዎች 2:6-23

ወደ ቈላስይስ ሰዎች 2:6-23 መቅካእኤ

እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ አብዝታችሁ ምስጋናን በማቅረብ እንደ ተማራችሁት ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፤ በእምነትም ጽኑ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ መሠረታዊው የዓለም ረቂቅ መንፈስ በፍልስፍናና በከንቱ መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠንቀቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል ተገልጦ ይኖራልና፤ የአለቅነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። በክርስቶስ መገረዝ የሥጋዊውን አካል በመግፈፍ በሰው እጅ ባልተከናወነ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሞታችሁ የነበራችሁትን በደላችንን ሁሉ ይቅር ባለን ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ እርሱም ይፃረረንና ይቃወመን የነበረውን በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ በመስቀልም ላይ ቸንክሮ ከእኛ አስወገደው፤ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ በመስቀሉ ድል በመንሣት እነርሱን በይፋ አጋለጣቸው። እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ወደ ፊት ለሚመጡት ነገሮች እንደ ጥላ ናቸውና፤ እውነቱ የሚገኘው ግን በክርስቶስ ነው። ራስን ማዋረድና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባየውም ራእይ ላይ በጽኑ እየተመረኮዘ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ የሚያድገውን አካል ሁሉ የሚንከባከበውን በመገጣጠምያዎቹና በጅማቶቹ አብሮ የሚያስተሳስረውን ራስ በጽኑ ሳይዝ ማንም አያውግዛችሁ። ከመሠረታዊው የዓለም ረቂቅ መንፈስ ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ ከዓለም እንዳልተለያችሁ ዓይነት ኑሮ ለምን ትኖራላችሁ? ለምንስ እንደነዚህ ላሉት ትእዛዞች ትገዛላችሁ? እነርሱም፦ “አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ” የሚሉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ትእዛዛት በጥቅም ላይ በመዋላቸው የሚጠፉትን ነገሮች የሚጠቁሙ ናቸው፤ እንዲያው በቀላሉ የሰው ትእዛዛትና አስተምሮ ናቸው። እነዚህም በገዛ ፈቃድ የሚደረግ አምልኮንና ራስን ማዋረድ ሥጋንም የመጨቆን ጥበብ ያላቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅሙም።