ዳንኤል 5
5
በግድግዳው ላይ የታየው ጽሕፈት
1ንጉሥ ቤልሻዛር ለሺሕ መኳንንቱ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በሺሑም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር። 2ቤልሻዛር የወይን ጠጁን እየጠጣ ሳለ፣ አባቱ#5፥2 ወይም አያት፤ ወይም ቀዳሚ ዘር እንዲሁም 11፣ 13 እና 18 ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ያመጣቸውን የወርቅና የብር መጠጫዎችን እርሱና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ እንዲያመጡለት አዘዘ። 3ከዚያም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከአምላክ ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን የወርቅ መጠጫዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹም ጠጡባቸው። 4የወይን ጠጁንም እየጠጡ የወርቅና የብር፣ የናስ፣ የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገኑ።
5በድንገትም የሰው እጅ ጣቶች ታዩ፤ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በመቅረዙ ትይዩ ባለው ግድግዳ ልስን ላይ ጻፉ፤ ንጉሡም ይጽፍ የነበረውን እጅ አየ፤ 6በዚያ ጊዜ ንጉሡ በድንጋጤ ተሞላ፤ ፊቱም ተለዋወጠ፤ እጆቹና እግሮቹ ከዱት፤ ጕልበቶቹም ተብረከረኩ።
7ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ አስማተኞችን፣ ኮከብ ቈጣሪዎችንና#5፥7 ወይም ከለዳውያን፤ እንዲሁም 11 መተተኞችን እንዲያስገቡለት አዘዘ፤ ለባቢሎናውያኑ ጠቢባን እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ጽሕፈት አንብቦ ትርጕሙን የሚነግረኝን ሐምራዊ መጐናጸፊያ አለብሰዋለሁ፤ የወርቅ ሐብልም በዐንገቱ ላይ አጠልቅለታለሁ፤ በመንግሥቴም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል።”
8ከዚያም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ሊያነብብም ሆነ ትርጕሙ ምን እንደ ሆነ ለንጉሡ ሊነግር የሚችል ማንም አልነበረም። 9ንጉሥ ቤልሻዛር ከፊት ይልቅ ፈራ፤ ፊቱም እጅግ ተለወጠ፤ መኳንንቱም ግራ ገብቷቸው ተደናገጡ።
10ንግሥቲቱም#5፥10 ወይም የንጉሡ እናት የንጉሡንና የመኳንንቱን ድምፅ ሰምታ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገባች፤ እንዲህም አለች፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ አትደንግጥ፤ ፊትህም አይለዋወጥ! 11በመንግሥትህ ውስጥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት አንድ ሰው አለ፤ ይህ ሰው በአባትህ ዘመን እንደ አማልክት ጥበብና ማስተዋል፣ ዕውቀትም የሞላበት ሆኖ ተገኝቷል፤ አባትህ ንጉሥ ናቡከደነፆርም የጠንቋዮች፣ የአስማተኞች፣ የኮከብ ቈጣሪዎችና የመተተኞች አለቃ አደረገው። 12ንጉሡ ብልጣሶር ብሎ የጠራው ይህ ዳንኤል መልካም መንፈስ፣ ዕውቀትና ማስተዋል ያለው ሆኖ ተገኘ፤ ሕልምን የመተርጐም፣ ዕንቈቅልሽን የመፍታትና የተሰወረውን የመግለጥ ልዩ ችሎታም ነበረው። ስለዚህ ዳንኤልን አስጠራ፤ እርሱም የጽሕፈቱን ትርጕም ይነግርሃል።”
13ዳንኤልንም ወደ ንጉሡ አቀረቡት፤ ንጉሡም እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ማርኮ ካመጣቸው መካከል አንዱ የሆንኸው ዳንኤል አንተ ነህን? 14የአማልክት መንፈስ በውስጥህ እንዳለ፣ ዕውቀት፣ ማስተዋልና ልዩ ጥበብ እንዳለህ ሰምቻለሁ። 15ይህን ጽሕፈት አንብበው ትርጕሙ ምን እንደ ሆነ ይነግሩኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች በፊቴ ቀርበው ነበር፤ ነገር ግን ሊገልጡት አልቻሉም። 16አንተ ግን መተርጐምና አስቸጋሪ የሆነውን ነገር መፍታት እንደምትችል ሰምቻለሁ። ይህን ጽሕፈት አንብበህ ትርጕሙን ብትነግረኝ፣ ሐምራዊ መጐናጸፊያ ያለብሱሃል፤ የወርቅ ሐብል በዐንገትህ ያጠልቁልሃል፤ የመንግሥት ሦስተኛ ገዥም ትደረጋለህ።”
17ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ስጦታዎችህን ለራስህ አድርግ፤ ሽልማቶችህንም ለሌላ ሰው ስጥ፤ ይሁን እንጂ ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ፤ ትርጕሙ ምን እንደ ሆነም እነግረዋለሁ።
18“ንጉሥ ሆይ፤ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር ገናናነትንና ታላቅነትን፣ ክብርንና ግርማን ሰጠው። 19ከሰጠው ታላቅ ሥልጣን የተነሣ ሕዝቦችና መንግሥታት፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችም ሁሉ ተንቀጠቀጡለት፤ ፈሩትም። ንጉሡም ሊገድል የፈለገውን ይገድል፣ ሊያድን የፈለገውን ያድን፣ ሊሾም የፈለገውን ይሾም፣ ሊያዋርድ የፈለገውንም ያዋርድ ነበር። 20ነገር ግን ልቡ በትዕቢት በጸናና በእብሪት በተሞላ ጊዜ ከዙፋኑ ተወገደ፤ ክብሩም ተገፈፈ። 21ከሰው መካከል ተሰደደ፤ የእንስሳም አእምሮ ተሰጠው፤ ከዱር አህዮች ጋራ ኖረ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ፤ ልዑል አምላክ በሰዎች መንግሥታት ላይ እንደሚገዛና እነርሱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስኪያውቅ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ።
22“ቤልሻዛር ሆይ፤ አንተ ልጁ#5፥22 ወይም ዘሩ ወይም ምትክ ሆነህ ይህን ሁሉ ብታውቅም፣ ራስህን ዝቅ አላደረግህም፤ 23ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ፣ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ የመቅደሱን መጠጫዎች አስመጣህ፤ አንተና መኳንንትህ፣ ሚስቶችህና ቍባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ማየት፣ መስማት፣ ማስተዋልም የማይችሉትን የብርና የወርቅ፣ የናስና የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገንህ። ሕይወትህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላከበርህም። 24ስለዚህ እርሱ ጽሕፈቱን የጻፈውን እጅ ላከ።
25“የተጻፈውም ጽሕፈት፣
‘ማኔ፣ ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ’#5፥25 በአራማይክ ኢፋርሲን ይኸውም ፋርሲንና ማለት ነው።
ይላል።
26“የቃሉም ትርጕም ይህ ነው፤
“ማኔ#5፥26 ማኔ ማለት የተቍጠረ ወይም ምናን (ራሱን የቻለ አንድ የገንዘብ ክፍል) ማለት አምላክ የመንግሥትህን ዘመን ቈጠረው፤ ወደ ፍጻሜም አደረሰው ማለት ነው።
27“ቴቄል#5፥27 ቴቄል ማለት የተመዘነ ወይም ሰቅል ሊሆን ይችላል። ማለት በሚዛን ተመዘንህ፤ ቀለህም ተገኘህ፣ ማለት ነው።
28“ፋሬስ#5፥28 ፋሬስ የፋርሲን ነጠላ ቍጥር ሲሆን ተከፈለ ወይም ፐርሺያ ወይም የሰቅል እኩሌታ ማለት ሊሆን ይችላል። ማለት መንግሥትህ ተከፈለ፣ ለሜዶናውያንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠ ማለት ነው።”
29ከዚህ በኋላ በቤልሻዛር ትእዛዝ ዳንኤልን ሐምራዊ መጐናጸፊያ አለበሱት፣ የወርቅ ሐብል በዐንገቱ ላይ አጠለቁለት፤ የመንግሥቱም ሦስተኛ ገዥ ሆኖ ተሾመ።
30በዚያ ሌሊት የባቢሎናውያን#5፥30 ወይም ከለዳውያን ንጉሥ ቤልሻዛር ተገደለ፤ 31የስድሳ ሁለት ዓመት ዕድሜ የነበረው ሜዶናዊው ዳርዮስም መንግሥቱን ወሰደ።
Currently Selected:
ዳንኤል 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.