ዘዳግም 1
1
እስራኤል ከኮሬብ እንዲነሡ የተሰጠ ትእዛዝ
1ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ዓረባ በተባለው ምድረ በዳ ከሱጵ ትይዩ፣ በፋራንና በጦፌል፣ በላባን፣ በሐጼሮትና በዲዛሃብ መካከል ሳሉ፣ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2(በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ዐሥራ አንድ ቀን ያስሄዳል)።
3በአርባኛው ዓመት፣ በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን እስራኤላውያንን በሚመለከት እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ሙሴ ለእነርሱ ነገራቸው። 4ይህ የሆነው በሐሴቦን ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንና በአስታሮት ይገዛ የነበረውን የዐግን ንጉሥ ባሳንን በኤድራይ ድል ካደረገ በኋላ ነው።
5ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ በሞዓብ ምድር ሳሉ፣ ሙሴ ይህን ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤
6 እግዚአብሔር አምላካችን በኮሬብ እንዲህ አለን፤ “እነሆ፤ በዚህ ተራራ ለረዥም ጊዜ ቈይታችኋል። 7ሰፈር ነቅላችሁ ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ጕዞ ቀጥሉ፤ ከዚያም በዓረባ፣ በተራሮቹ፣ በምዕራብ ኰረብቶች ግርጌ፣ በኔጌብና በባሕሩ ዳርቻ ወዳሉት አጐራባች ሕዝቦች ሁሉ ሂዱ፤ እንዲሁም ወደ ከነዓናውያን ምድርና ወደ ሊባኖስ፣ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ዝለቁ። 8እነሆ፤ ይህችን ምድር ሰጥቻችኋለሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ፣ ከእነርሱም በኋላ ለዘሮቻቸው ሊሰጥ የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ ውረሱ።”
የመሪዎች መሾም
9እኔም በዚያ ጊዜ እንዲህ አልኋችሁ፤ “ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤ 10አምላካችሁ እግዚአብሔር ቍጥራችሁን ጨምሯል፤ ስለዚህ ዛሬ እናንተ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችኋል። 11አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ሺሕ ጊዜ ያብዛችሁ፣ በሰጠውም ተስፋ መሠረት ይባርካችሁ! 12ይሁን እንጂ ችግራችሁን፣ ሸክማችሁንና ክርክራችሁን ሁሉ ብቻዬን እንዴት አድርጌ መሸከም እችላለሁ? 13ጥበበኞችን፣ አስተዋዮችንና የተከበሩ ሰዎችን ከየነገዳችሁ ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ እሾማቸዋለሁ።”
14እናንተም፣ “ይደረግ ዘንድ ያቀረብኸው ሐሳብ መልካም ነው” ብላችሁ መለሳችሁልኝ።
15ስለዚህ እኔም የየነገዶቻችሁን አለቆች ጥበበኞችንና የተከበሩትን ሰዎች ተቀብዬ፣ ሻለቆች፣ መቶ አለቆች፣ ዐምሳ አለቆችና ዐሥር አለቆች እንዲሁም የየነገዱ ሹማምት በማድረግ በእናንተ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ሾምኋቸው። 16በዚያ ጊዜም ዳኞቻችሁን እንዲህ ስል አዘዝኋቸው፤ “በወንድሞቻችሁ መካከል የሚነሣውን ክርክር ያለ አድልዎ እዩት፤ ሙግቱ ወንድማማች በሆኑ እስራኤላውያን መካከል ወይም በአንድ እስራኤላዊና በመጻተኛ መካከል ቢሆን፣ በጽድቅ ፍረዱ። 17በፍርድ አድልዎ አታድርጉ፤ ትልቁንም ትንሹንም እኩል እዩ፤ ፍርድ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ ማንኛውንም ሰው አትፍሩ። ከዐቅማችሁ በላይ የሆነውን ሁሉ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔ አየዋለሁ።” 18በዚያ ጊዜ ማድረግ የነበረባችሁን ሁሉ ነገርኋችሁ።
የሰላዮች መላክ
19ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ ተነሥተን እንዳያችሁት በዚያ ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ ዐልፈን፣ በኰረብታማው በአሞራውያን አገር በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን። 20እኔም፣ እንዲህ አልኋችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ደርሳችኋል፤ 21እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ሰጥቷችኋል፤ አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በነገራችሁ መሠረት ውጡ፤ ውረሷትም፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም።”
22ከዚያም ሁላችሁ ወደ እኔ መጥታችሁ፣ “ምድሪቱን እንዲሰልሉልን ሰዎች አስቀድመን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያ የሚያደርሰንን መንገድና የምንሄድባቸውን ከተሞች በማጥናት ተመልሰው ይነግሩናል” አላችሁ።
23ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ እኔም ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በማድረግ ከእናንተ ዐሥራ ሁለት ሰዎች መረጥሁ። 24እነርሱም ተነሥተው ወደ ኰረብታማው አገር ከወጡ በኋላ ወደ ኤሽኮል ሸለቆ መጥተው ምድሪቱን ሰለሉ። 25ከምድሪቱም ፍሬ ወደ እኛ ይዘው በመምጣት፣ “አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት” ብለው ነገሩን።
በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ
26እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ። 27በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጕረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብጽ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው። 28ታዲያ ወዴት መሄድ እንችላለን? ወንድሞቻችን፣ ‘ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎችና ቁመተ ረዣዥሞች፣ ከተሞቹም ትልልቆችና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤ እንዲያውም በዚያ የዔናቅን ልጆች አይተናቸዋል’ ሲሉ እንድንፈራ አድርገውናል።”
29እኔም አልኋችሁ፤ “አትሸበሩ፤ አትፍሯቸውም። 30በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ዐይናችሁ እያየ በግብጽ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፣ አሁንም ለእናንተ ይዋጋል፤ 31በምድረ በዳው እንደ አደረገው ሁሉ። በዚያም አባት ልጁን እንደሚሸከም፣ እናንተን አምላካችሁ እግዚአብሔር እዚህ ስፍራ እስክትደርሱ በመጣችሁበት መንገድ ሁሉ እንዴት እንደ ተሸከማችሁ አይታችኋል።”
32ይህም ሆኖ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር አልታመናችሁም፤ 33በጕዞ ላይ ሳላችሁ የምትሰፍሩባቸውን ቦታዎች ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት እርሱ ሌሊት በእሳት፣ ቀን በደመና ይመራችሁ ነበር።
34 እግዚአብሔርም እናንተ ያላችሁትን በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ ማለም፤ 35“ለቀደሙት አባቶቻችሁ ለመስጠት የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር፣ ከዚህ ክፉ ትውልድ አንድም ሰው አያያትም፤ 36ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በቀር የሚያያት የለም፤ እርሱ ያያታል፤ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ ስለ ተከተለ፣ የረገጣትን ምድር ለርሱና ለዘሮቹ እሰጣለሁ።”
37በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔር እኔን ተቈጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “አንተም ብትሆን አትገባባትም። 38ረዳትህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ይገባባታል፤ ምድሪቱን እንዲወርሱ እስራኤልን የሚመራ እርሱ ስለ ሆነ፣ አበረታታው። 39ይማረካሉ ያላችኋቸው ታናናሾች፣ ክፉና በጎውን ለይተው የማያውቁት ልጆቻችሁ ምድሪቱን ይገቡባታል፤ ለእነርሱም እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሷታል። 40እናንተ ግን፣ ተመልሳችሁ ወደ ቀይ ባሕር#1፥40 ዕብራይስጡ፣ ያም ሳውፍ ይለዋል፤ ይኸውም፣ የደንገል ባሕር ማለት ነው። የሚወስደውን መንገድ ይዛችሁ ወደ ምድረ በዳው ተጓዙ።”
41እናንተ፣ “በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርተናል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ባዘዘንም መሠረት ወጥተን እንዋጋለን” ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ወደ ተራራማው አገር መሄድ ቀላል መስሎ ስለ ታያችሁ፣ እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን ታጥቃችሁ ተነሣችሁ።
42 እግዚአብሔር ግን፣ “ ‘እኔ ከእናንተ ጋራ አልሆንምና ወጥታችሁ እንዳትዋጉ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትነሣላችሁ’ ብለህ ንገራቸው” አለኝ።
43እኔም ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁም፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐምፃችሁ፣ በትዕቢታችሁ ወደ ተራራማው አገር ዘመታችሁ። 44በእነዚያ በተራራማው አገር የሚኖሩት አሞራውያን ሊወጓችሁ ወጡ፤ እንደ ንብ ሰራዊትም ሆነው አባረሯችሁ፤ ከሴይር አንሥቶ እስከ ሖርማ ድረስ አሳድደው መቷችሁ። 45እናንተም ተመልሳችሁ መጥታችሁ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሳችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ልቅሷችሁን አልሰማም፤ አላደመጣችሁምም። 46ስለዚህ ያን ያህል ጊዜ በማጥፋት በቃዴስ ብዙ ቀን ቈያችሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.