ዘዳግም 2
2
በምድረ በዳ መንከራተት
1ከዚያም እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት ተመለስን፤ ቀይ ባሕርን#2፥1 ዕብራይስጡ፣ ያም ሳውፍ ይለዋል፤ ይኸውም የደንገል ባሕር ማለት ነው። ይዘን ወደ ምድረ በዳው ተጓዝን፤ በሴይር ኰረብታማ አገር ዙሪያ ለረዥም ጊዜ ተንከራተትን።
2ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ 3“በዚህ በኰረብታማ አገር ዙሪያ እስኪበቃችሁ ተንከራታችኋል፤ አሁን ግን ወደ ሰሜን ተመለሱ። 4ለሕዝቡም እነዚህን ትእዛዞች ስጣቸው፤ ‘ሴይር በሚኖሩት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ዘሮች ግዛት ዐልፋችሁ ትሄዳላችሁ፤ እነርሱ ይፈሯችኋል፤ ቢሆንም ከፍ ያለ ጥንቃቄ አድርጉ። 5ከየትኛውም ምድራቸው ላይ ለጫማችሁ መርገጫ ታኽል እንኳ መሬት ስለማልሰጣችሁ፣ ለጦርነት አታነሣሧቸው። ኰረብታማውን የሴይርን አገር ርስት አድርጌ ለዔሳው ሰጥቼዋለሁ። 6ከዚያ ለምትበሉት ምግብም ሆነ ለምትጠጡት ውሃ በጥሬ ብር ትከፍሏቸዋላችሁ።’ ”
7አምላካችሁ እግዚአብሔር በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኳችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጕዞ ጠብቋችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።
8ስለዚህ በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮች የሆኑ ወንድሞቻችንን ዐልፈናቸው ሄድን። ከኤላትና ከዔጽዮንጋብር ከሚመጣው ከዓረባ መንገድ ተመልሰን፣ በሞዓብ ምድረ በዳ መንገድ ተጓዝን።
9ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ከሞዓባውያን ምድር አንዳችም መሬት ስለማልሰጣችሁ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሧቸው፤ ዔርን ለሎጥ ዘሮች ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ” አለኝ።
10በዚያም ጠንካራና ቍጥራቸው የበዛ እንዲሁም እንደ ዔናቃውያን ረዣዥም የሆኑ ኤሚማውያን ይኖሩ ነበር። 11እነዚህም እንደ ዔናቃውያን ሁሉ ራፋይማውያን ናቸው ተብለው ይገመቱ ነበር፤ ሞዓባውያን ግን ኤሚማውያን ብለው ይጠሯቸዋል። 12ሖሪውያን ቀድሞ በሴይር ይኖሩ ነበር፤ የዔሳው ዘሮች ግን ከዚያ አሳድደው አስወጧቸው። እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሰጠው ምድር ላይ እስራኤል እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህም ሖሪውያንን ከፊታቸው አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።
13ከዚያም እግዚአብሔር “አሁኑኑ ተነሡና የዘሬድን ደረቅ ወንዝ ተሻገሩ” አለን፤ እኛም ወንዙን ተሻገርን።
14ቃዴስ በርኔን ከለቀቅንበት ጊዜ አንሥቶ የዘሬድን ደረቅ ወንዝ እስከ ተሻገርንበት ጊዜ ድረስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ዐለፈ። በዚያ ጊዜም ለጦርነት ብቁ የሆኑት የዚያ ትውልድ ወንዶች ሁሉ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ አስቀድሞ በማለው መሠረት ከሰፈሩ ፈጽመው ዐለቁ። 15ከሰፈር ፈጽሞ እስኪያጠፋቸውም ድረስ የእግዚአብሔር እጅ በእነርሱ ላይ ነበር።
16በሕዝቡ መካከል የነበሩት የመጨረሻዎቹ ተዋጊዎች ከሞቱ በኋላ፣ 17እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ 18“የሞዓብ ዳርቻ ዔርን ዛሬውኑ ታልፋላችሁ። 19ከየትኛውም የአሞናውያን ምድር ለእናንተ ርስት ስለማልሰጣችሁ፣ አሞናውያን ዘንድ በደረሳችሁ ጊዜ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሧቸው። ያን ቦታ ርስት አድርጌ ለሎጥ ዘሮች ሰጥቻቸዋለሁ።”
20ያም ደግሞ በዚያ ይኖሩ የነበሩት የራፋይማውያን ምድር እንደ ሆነ ይቈጠር ነበር፤ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሯቸው ነበር። 21ዘምዙማውያን ብርቱዎች፣ ቍጥራቸው የበዛና እንደ ዔናቃውያን ቁመተ ረዣዥሞች ነበሩ፤ እግዚአብሔር ከእነርሱ ፊት አጠፋቸው፤ እነርሱም አሳደዷቸው፤ በምትካቸውም ሰፈሩበት። 22እግዚአብሔር ሖሪውያንን ከፊታቸው ባጠፋ ጊዜ፣ በሴይር ለሚኖሩት የዔሳው ዘሮች ያደረገው ይህንኑ ነበር። እነርሱም አሳድደው በማስወጣት ባስለቀቁት ስፍራ ላይ እስከ ዛሬ ይኖራሉ። 23እስከ ጋዛ ድረስ ባሉት መንደሮች የኖሩትን ኤዋውያን በተመለከተም፣ ከቀፍቶር#2፥23 ቀርጤስ ናት ወጥተው የመጡት ከቀፍቶሪማውያን፣ እነርሱን አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።
የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን ድል መነሣት
24“አሁኑኑ ተነሡና የአርኖንን ወንዝ ተሻገሩ፤ እነሆ፤ የሐሴቦንን ንጉሥ፣ አሞራዊውን ሴዎንንና አገሩን በእጃችሁ ሰጥቻችኋለሁ፤ ምድሩን መውረስ ጀምሩ፤ ጦርነት ግጠሙት። 25ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ፣ ማስደንገጣችሁና ማስፈራታችሁ እንዲያድርባቸው ከዚህች ከዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ። ስለ እናንተ ሰምተው ይርበተበታሉ፤ ከእናንተ የተነሣም ይጨነቃሉ።”
26ከቅዴሞት ምድረ በዳም ለሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን የሰላም ቃል እንዲያደርሱለት እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላክሁ፤ 27“በአገርህ አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን፤ ከዋናው መንገድ አንወጣም፤ ቀኝም ግራም አንልም። 28የምንበላውን ምግብ፣ የምንጠጣውንም ውሃ በጥሬ ብር ሽጥልን። በእግር እንድናልፍ ብቻ ፍቀድልን፤ 29በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮችና በዔር የሚኖሩ ሞዓባውያን እንዳደረጉልን ሁሉ፣ አንተም አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን እስክንሻገር ድረስ እንደዚሁ አድርግልን።” 30ይሁን እንጂ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን እንድናልፍ አልፈቀደልንም፤ ምክንያቱም አምላካችሁ እግዚአብሔር አሁን እንዳደረገው ሁሉ እርሱን በእጃችሁ አሳልፎ ለመስጠት መንፈሱን አደንድኖት፣ ልቡንም አጽንቶት ነበር።
31 እግዚአብሔርም፣ “እነሆ፤ ሴዎንንና አገሩን ለእናንተ አሳልፌ ልሰጣችሁ ተነሥቻለሁ፤ አሁንም እርሱን አሸንፋችሁ ምድሩን ለመውረስ ተነሡ” አለኝ።
32ሴዎንና መላው ሰራዊቱ በያሀጽ ጦርነት ሊገጥሙን በወጡ ጊዜ፣ 33አምላካችን እግዚአብሔር በእጃችን ላይ ጣለው፤ እኛም፣ እርሱን ከወንድ ልጆቹና ከመላው ሰራዊቱ ጋራ አንድ ላይ መታነው። 34በዚያ ጊዜ ከተሞቹን በሙሉ ወስደን የሚኖሩባቸውን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆቻቸውን ጭምር ፈጽመን አጠፋናቸው#2፥34 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።፤ አንዳቸውንም በሕይወት አላስቀረንም። 35ከብቶቻቸውንና ከየከተሞቻቸው ያገኘነውን ምርኮ ግን ለራሳችን አደረግን። 36በአርኖን ሸለቆ ጫፍ ካለችው ከአሮዔርና በሸለቆው ውስጥ ከምትገኘዋ ከተማ አንሥቶ እስከ ገለዓድ ካሉት ከተሞች አንዳቸውም እንኳ ሊገቱን አልቻሉም። አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉንም አሳልፎ ሰጠን። 37ይሁን እንጂ አምላካችን እግዚአብሔር በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ ወደ ማንኛውም የአሞናውያን ምድር ወይም በያቦቅ ወንዝ መውረጃ ወዳለው ምድር ወይም ደግሞ በኰረብቶች ወዳሉት ከተሞች ዙሪያ ዐልፋችሁ አልሄዳችሁም።
Currently Selected:
ዘዳግም 2: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.