የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘዳግም 3

3
የባሳን ንጉሥ የዐግ መሸነፍ
1ከዚያም ተመልሰን ወደ ባሳን የሚወስደውን መንገድ ይዘን ወጣን፤ የባሳን ንጉሥ ዐግም ከመላው ሰራዊቱ ጋራ ሆኖ በኤድራይ ጦርነት ሊገጥመን ተነሣ። 2እግዚአብሔር፣ “እርሱን፣ መላው ሰራዊቱንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ስለ ሰጠሁህ፣ አትፍራው፤ ሐሴቦንን ይገዛ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ ያደረግህበትን በርሱም ላይ አድርግበት” አለኝ።
3ስለዚህ አምላካችን እግዚአብሔር የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመላው ሰራዊቱ ጋራ ሁሉ እንደዚሁ በእጃችን ላይ ጣላቸው፤ እኛም አንድ እንኳ በሕይወት ሳናስቀር አጠፋናቸው። 4በዚያ ጊዜ ከተሞቹን ሁሉ ያዝን፤ የዐግ ግዛት ከሆነው፣ በባሳን ከሚገኘው ከጠቅላላው የአርጎብ ክልል ስድሳ ከተሞች ውስጥ፣ እኛ ያልያዝነው አንድም ከተማ አልነበረም። 5እነዚህ ከተሞች ሁሉ ከፍ ባሉ ቅጥሮች፣ በመዝጊያዎችና በመወርወሪያዎች የተመሸጉ ነበሩ፤ እንዲሁም ቅጥር የሌላቸው አያሌ መንደሮች ነበሩ። 6በእያንዳንዱ ከተማ ያሉትን ወንዶቹን፣ ሴቶቹንና ልጆቻቸውን ጭምር በማጥፋት፣ በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግነው ሁሉ፣ እነዚህንም ፈጽመን ደመሰስናቸው#3፥6 የ2፥34 አማራጭ ትርጕም ይመ።7ከብቱን በሙሉና ከየከተሞቻቸው የማረክነውን ሁሉ ግን ለራሳችን አደረግን።
8ስለዚህ በዚያ ጊዜ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የሚገኘውን፣ ከአርኖን ሸለቆ እስከ አርሞንዔም ተራራ ያለውን ግዛት፣ ከእነዚህ ከሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ላይ ወሰድንባቸው። 9አርሞንዔምን፣ ሲዶናውያን ሢርዮን ብለው ሲጠሩት፣ አሞራውያን ግን ሳኔር ይሉታል። 10በከፍታው ቦታ ላይ የሚገኙትን ከተሞች በሙሉ፣ ገለዓድን እንዳለ፣ እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ያለውን ባሳንን ሁሉ እንዲሁም በባሳን ውስጥ የሚገኙትን የዐግ ግዛት ከተሞች በእጃችን አደረግን። 11ከራፋይማውያን ወገን የተረፈ የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻ ነበር። ዐልጋው#3፥11 ወይም፣ ድንጋይ ተጠርቦ የተዘጋጀ የሬሳ ሣጥን ከብረት የተሠራ ቁመቱም ዘጠኝ ክንድ፣ ስፋቱ ደግሞ አራት ክንድ#3፥11 ቁመቱ 4 ሜትር ስፋቱ 1.8 ሜትር ያህል ነው። ነበር። ይህም እስካሁን በአሞናውያን ከተማ በረባት ይገኛል።
እስራኤላውያን ምድሪቱን መከፋፈላቸው
12በዚያ ጊዜ ከያዝነው ምድር ላይ በአርኖን ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር አንሥቶ በስተሰሜን ያለውን ግዛት፣ በተጨማሪም ኰረብታማውን የገለዓድ አገር እኩሌታ ከነከተሞቹ ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን ሰጠኋቸው። 13ቀሪውን የገለዓድ ምድርና የዐግ ግዛት የሆነውን ባሳንን በሙሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ። በባሳን የሚገኘው መላው የአርጎብ ክልል የራፋይማውያን ምድር በመባል ይታወቅ ነበር። 14ከምናሴ ነገድ የሆነው ኢያዕር፣ እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ወሰን ድረስ የሚገኘውን መላውን የአርጎብ ምድር ወሰደ፤ ምድሪቱም በስሙ ተጠራች#3፥14 ወይም፣ የኢያዕር መኖሪያ ተብላ ተጠራች፤ ከዚሁ የተነሣ ባሳን እስከ ዛሬ ድረስ ሓቦት ኢያዕር ትባላለች። 15ገለዓድንም ለማኪር ሰጠሁት። 16ነገር ግን የሸለቆውን እኩሌታ ወሰን በማድረግ ከገለዓድ አንሥቶ እስከ አርኖን ሸለቆ፣ ከዚያም የአሞናውያን ድንበር እስከ ሆነው እስከ ያቦቅ ወንዝ ያለውን ግዛት ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን ሰጠኋቸው። 17የምዕራቡ ወሰን፣ በዓረባ የሚገኘው ዮርዳኖስ ሲሆን፣ ይኸውም ከፈስጋ ተረተሮች በታች፣ ከኪኔሬት አንሥቶ የጨው ባሕር#3፥17 ይኸውም የሙት ባሕር ነው። እስከሚባለው እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ ነው።
18በዚያ ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ለእናንተ ሰጥቷችኋል፤ ይሁን እንጂ የአካል ብቃት ያላቸው ሰዎቻችሁ ሁሉ ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤላውያን ፊት በመቅደም መሻገር አለባቸው። 19ሆኖም ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ፣ (ብዙ ከብቶች እንዳሏችሁም ስለማውቅ) ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ውስጥ ይቈዩ፤ 20ይኸውም፣ እግዚአብሔር ለእናንተ እንዳደረገው ሁሉ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፋቸውና አምላካችሁ እግዚአብሔር ከዮርዳኖስ ማዶ የሚሰጣቸውን ምድር እነርሱም እንደዚሁ እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያ በኋላ እያንዳንዳችሁ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።”
ሙሴ ዮርዳኖስን እንዳይሻገር መከልከሉ
21በዚያ ጊዜ ኢያሱን እንዲህ ስል አዘዝሁት፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለቱ ነገሥታት ላይ ያደረገውን ሁሉ በገዛ ዐይንህ አይተሃል፤ አሁንም ዐልፈህ በምትሄድባቸው መንግሥታት ላይ ሁሉ እግዚአብሔር ይህንኑ ይደግመዋል። 22አምላካችሁ እግዚአብሔር ራሱ ይዋጋላችኋልና አትፍሯቸው።”
23በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን እንዲህ ብዬ ለመንሁት፤ 24“ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ታላቅነትህንና ብርቱ ክንድህን ለእኔ ለባሪያህ እነሆ ማሳየት ጀምረሃል፤ ለመሆኑ በሰማይም ሆነ በምድር፣ አንተ የምታደርጋቸውን ሥራዎችና ታላላቅ ድርጊቶች መፈጸም የሚችል አምላክ ማነው? 25አሁንም ከዮርዳኖስ ማዶ ያለችውን ያችን መልካሚቱን ምድር፣ ውብ የሆነችውን ኰረብታማ አገርና ሊባኖስን እንዳይ ፍቀድልኝ።”
26 እግዚአብሔር ግን በእናንተ ሰበብ ተቈጥቶኝ ነበርና አልሰማኝም፤ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ይበቃል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ስለዚህ ነገር አታንሣብኝ። 27ወደ ፈስጋ ተራራ ጫፍ ውጣ፤ ወደ ምዕራብና ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅም ተመልከት። አንተ ዮርዳኖስን ስለማትሻገር፣ ምድሪቱን በዐይንህ ብቻ እያት። 28ነገር ግን ሕዝቡን መርቶ በማሻገር የምታያትን ምድር እንዲወርሱ የሚያደርጋቸው ስለ ሆነ፣ ኢያሱን ላከው፤ አደፋፍረው፤ አበረታታውም።” 29ስለዚህ እኛ በቤተ ፌጎር አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ ቈየን።

Currently Selected:

ዘዳግም 3: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ