ዘዳግም 4
4
ሙሴ እስራኤላውያን እንዲታዘዙ ማስጠንቀቁ
1አሁንም እስራኤል ሆይ፤ በሕይወት እንድትኖሩ፣ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር እንድትገቡና እንድትወርሱ የማስተምራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ ጠብቋቸውም። 2ባዘዝኋችሁ ላይ አትጨምሩ፤ ከርሱም አትቀንሱ፤ ነገር ግን የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ጠብቁ።
3 እግዚአብሔር በበኣል ፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከመካከላችሁ በኣል ፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቷቸዋል፤ 4አምላካችሁን እግዚአብሔርን የተከተላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው እስከ ዛሬ በሕይወት አላችሁ።
5ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ። 6በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ “በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው” ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና። 7በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ እንደ ሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው? 8ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ ጽድቅ የሆነ ሥርዐትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው?
9ዐይኖቻችሁ ያዩአቸውን ነገሮች እንዳትረሱ፣ ደግሞም በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ብቻ ተጠንቀቁ፣ ነቅታችሁም ራሳችሁን ጠብቁ። እነዚህን ለልጆቻችሁና ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስተምሯቸው። 10“በምድሪቱ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ እኔን ማክበር እንዲማሩ፣ ለልጆቻቸውም እንዲያስተምሩ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ ሕዝቡን በፊቴ ሰብስብ” ባለኝ ጊዜ፣ በኮሬብ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት የቆማችሁበትን ዕለት አስታውሱ። 11ተራራው በጥቍር ደመናና በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ ሳለ ነበልባሉ ሰማይ እስከሚደርስ ድረስ በተቃጠለ ጊዜ መጥታችሁ ከተራራው ግርጌ ቆማችሁ። 12ከዚያም እግዚአብሔር በእሳቱ ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ እናንተም የቃሉን ድምፅ ሰማችሁ፤ መልክ ግን አላያችሁም፤ ድምፅ ብቻ ነበርና። 13እርሱ ኪዳኑን ይኸውም እንድትከተሏቸው ያዘዛችሁን ዐሥርቱን ትእዛዛት ዐወጀላችሁ፤ ከዚያም በሁለት የድንጋይ ጽላት ላይ ጻፋቸው፤ 14ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ውስጥ የምትከተሏቸውን ሥርዐትና ሕግ እንዳስተምራችሁ በዚያ ጊዜ እግዚአብሔር አዘዘኝ።
ጣዖትን ማምለክ ስለ መከልከሉ
15 እግዚአብሔር በኮሬብ ተራራ ላይ በእሳት ውስጥ በተናገራችሁ ቀን ምንም ዐይነት መልክ ከቶ አላያችሁም፤ ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ 16ይኸውም እንዳትረክሱ፣ በወንድ ወይም በሴት መልክ በማንኛውም ዐይነት ምስል የተቀረጸ ጣዖት ለራሳችሁ እንዳታበጁ፣ 17ወይም በምድር ላይ የሚኖር የማናቸውንም እንስሳ ወይም በአየር ላይ የሚበርር የማናቸውንም ወፍ፣ 18ወይም በደረቱ የሚሳብ የማናቸውንም ፍጡር ወይም በውሃ ውስጥ የሚኖር የማናቸውንም ዓሣ ምስል እንዳታደርጉ ነው። 19ወደ ሰማይ ቀና ብለህ ፀሓይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን፣ የሰማይ ሰራዊትንም ሁሉ በምትመለከትበት ጊዜ፣ ወደ እነርሱ እንዳትሳብና እንዳትሰግድላቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰማይ በታች ላሉ ሕዝቦች ሁሉ ድርሻ አድርጎ የሰጣቸውንም ነገሮች እንዳታመልክ ተጠንቀቅ። 20እናንተን ግን ልክ ዛሬ እንደ ሆናችሁት ሁሉ ርስቱ ትሆኑለት ዘንድ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር እናንተን ከብረት ማቅለጫ ምድጃ፣ ከግብጽ አውጥቶ አመጣችሁ።
21በእናንተም ምክንያት እግዚአብሔር እኔን ተቈጣኝ፤ ዮርዳኖስንም እንዳልሻገርና አምላካችሁ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ወደ መልካሚቱ ምድር እንዳልገባ ማለ። 22እኔም በዚህች ምድር እሞታለሁ፤ ዮርዳኖስን አልሻገርም፤ እናንተ ግን ልትሻገሩ ነው፤ ያችንም መልካም ምድር ትወርሳላችሁ። 23አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ የገባውን ኪዳን እንዳትረሱ ተጠንቀቁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር የከለከለውን ጣዖት በማንኛውም ዐይነት መልክ ለራሳችሁ አታብጁ። 24አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚባላ እሳት፣ ቀናተኛም አምላክ ነውና።
25ልጆችንና የልጅ ልጆችን ከወለዳችሁና በምድሪቱም ላይ ለረዥም ጊዜ ከኖራችሁ በኋላ ራሳችሁን በማርከስ ማንኛውንም ዐይነት ጣዖት ብታበጁ፣ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ክፋት በማድረግ ለቍጣ ብታነሣሡት፣ 26ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትወርሷት ምድር ላይ ፈጥናችሁ እንደምትጠፉ በዚህ ቀን ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ ምስክሮች አድርጌ እጠራለሁ፤ በዚያ ቦታ ብዙ ዘመን አትኖሩም፤ ፈጽሞ ትጠፋላችሁ። 27እግዚአብሔር እናንተን በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፤ እግዚአብሔር በሚበትናችሁ አሕዛብ መካከል የምትተርፉት ጥቂቶቻችሁ ብቻ ናችሁ። 28እዚያም፣ ማየት ወይም መስማት ወይም መብላት ወይም ማሽተት በማይችሉ በሰው እጅ በተሠሩ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካላችሁ። 29ነገር ግን እዚያም ሆናችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ብትፈልጉት ታገኙታላችሁ። 30ስትጨነቅና ይህ ሁሉ ነገር ሲደርስብህ ያን ጊዜ፣ በኋለኞቹ ዘመናት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለህ፤ ትታዘዝለታለህም። 31አምላክህ እግዚአብሔር መሓሪ አምላክ ነውና አይተውህም ወይም አያጠፋህም፤ ወይም ደግሞ ለአባቶችህ በመሐላ ያጸናላቸውን ቃል ኪዳን አይረሳም።
እግዚአብሔር አምላክ ነው
32እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረበት ቀን ጀምሮ እናንተ ከመኖራችሁ በፊት ስለ ነበረው የቀድሞ ዘመን ጠይቁ፤ ከአንዱ የሰማይ ጫፍ እስከ ሌላው የሰማይ ጫፍ ድረስ ጠይቁ፤ እንደዚህ ያለ ታላቅ ነገር ከቶ ተደርጎ ወይስ እንደዚህ ዐይነት ነገር ከቶ ተሰምቶ ያውቃልን? 33ከእሳት ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደ እናንተ የሰማና በሕይወት የኖረ ከቶ ሌላ ሕዝብ አለን? 34አምላካችሁ እግዚአብሔር በዐይናችሁ እያያችሁ ለእናንተ በግብጽ እንዳደረገው ሁሉ በፈተና፣ በታምራዊ ምልክቶችና በድንቆች፣ በጦርነት፣ በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ ወይም በታላቅና በአስፈሪ ሥራዎች ከሌላ ሕዝብ መካከል አንድን ሕዝብ የራሱ ለማድረግ የቻለ አምላክ አለን?
35 እግዚአብሔር እርሱ አምላክ መሆኑን፣ ከርሱም በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን ታውቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እንድታዩ ተደረገ። 36ሊገሥጽህ ድምፁን ከሰማይ እንድትሰማ አደረገ፤ በምድርም ላይ አስፈሪ እሳቱን አሳየህ፤ ከእሳቱም ውስጥ ቃሉን ሰማህ። 37አባቶችህን ከመውደዱ የተነሣና ከእነርሱም በኋላ ዘራቸውን ስለ መረጠ፣ ከአንተ ጋራ በመሆን በታላቅ ኀይሉ ከግብጽ አወጣህ፤ 38ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ከፊትህ በማስወጣት ወደ ምድራቸው አስገብቶህ ለአንተ ርስት አድርጎ ለመስጠት ነው።
39እንግዲህ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እግዚአብሔር እርሱ አምላክ መሆኑን ዛሬ ዕወቅ፤ በልብህም ያዘው፤ ሌላም የለም። 40ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህም ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፣ ዛሬ እኔ የማዝዝህን ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ጠብቅ።
የመማፀኛ ከተሞች
4፥41-43 ተጓ ምብ – ዘኍ 35፥6-34፤ ዘዳ 19፥1-14፤ ኢያ 20፥1-9
41በዚያ ጊዜ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ሦስት ከተሞችን ለየ፤ 42ይኸውም የቈየ ጠላትነት ሳይኖር፣ በድንገት ባልንጀራውን የገደለ ማንኛውም ሰው ሸሽቶ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በመሄድ ሕይወቱን ማትረፍ ይችል ዘንድ ነው። 43ከተሞቹም በምድረ በዳው በከፍተኛ ቦታ ላይ የምትገኘው ቦሶር ለሮቤላውያን፣ በገለዓድ የምትገኘው ራሞት ለጋዳውያን፣ በባሳን ያለችው ጎላን ለምናሴያውያን ነበሩ።
ስለ ሕጉ የተሰጠ ማብራሪያ
44ሙሴ በእስራኤላውያን ፊት የደነገገው ሕግ ይህ ነው። 45ከግብጽ በወጡ ጊዜ ሙሴ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ምስክርነቶች፣ ሥርዐቶችና ሕጎች እነዚህ ናቸው፤ 46ይህም ከግብጽ በወጡ ጊዜ በሙሴና በእስራኤላውያን ድል በተደረገው፣ በሐሴቦን በነገሠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፣ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ በቤተ ፌጎር አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነው። 47ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለውን፣ የርሱን ምድርና የባሳንን ንጉሥ የዐግን፣ የሁለቱን አሞራውያን ነገሥታት ምድር ርስት አድርገው ወሰዱ። 48ይህም ምድር በአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሴዎን#4፥48 የዕብራይስጡና የሱርስቱ ትርጕም፣ ሢርዮን ይለዋል (ዘዳ 3፥9 ይመ) ተራራ ማለትም እስከ አርሞንዔም የሚደርስ ሲሆን፣ 49በዮርዳኖስ ምሥራቅ ያለውን ዓረባን በሙሉና ከፈስጋ ተረተር በታች ያለውን የዓረባ ባሕር#4፥49 ይኸውም የሙት ባሕር ነው። ያጠቃልላል።
Currently Selected:
ዘዳግም 4: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.