ዘዳግም 5
5
ዐሥርቱ ትእዛዛት
5፥6-21 ተጓ ምብ – ዘፀ 20፥1-17
1ሙሴ እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦
እስራኤል ሆይ፤ በዛሬዋ ዕለት በጆሯችሁ የምነግራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ አጥኗቸው፤ በጥንቃቄም ጠብቋቸው። 2አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቷል። 3እግዚአብሔር ይህን ቃል ኪዳን የገባውም ከአባቶቻችን ጋራ ሳይሆን፣ ዛሬ እዚህ በሕይወት ከምንገኘው ከእኛ ከሁላችን ጋራ ነው። 4እግዚአብሔር እናንተን በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ፊት ለፊት አነጋገራችሁ። 5እናንተ ግን እሳቱን በመፍራት ወደ ተራራው ስላልወጣችሁ፣ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ እነግራችሁ ዘንድ እኔ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ቆምሁ።
እርሱም እንዲህ አለ፤
6“ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።
7“ከእኔ በቀር#5፥7 ወይም፣ ከፊቴ ተብሎ መተርጐም ይችላል። ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።
8በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም ከምድር በታች ወይም ውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ነገሮች በማናቸውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ፤ 9አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸውም፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፣ የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። 10ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺሕ ትውልድ ፍቅርን የማሳይ ነኝ።
11የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አታንሣ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና።
12አምላክህ እግዚአብሔር ባዘዘህ መሠረት የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብረው። 13ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አከናውን። 14ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። በዚያ ቀን አንተም ሆንህ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ በሬህ፣ አህያህ ወይም ማንኛውም እንስሳህ ወይም ደግሞ በደጅህ ያለ እንግዳ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ። ይህም አንተ እንዳረፍህ ሁሉ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ እንዲያርፉ ነው። 15በግብጽ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ።
16አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር።
17አትግደል።
18አታመንዝር።
19አትስረቅ።
20በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
21የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ። በባልንጀራህ ቤትም ሆነ በመሬቱ፣ በወንድ ሆነ በሴት አገልጋዩ፣ በበሬውም ሆነ በአህያው ወይም የርሱ በሆነው በማንኛውም ነገር ላይ ዐይንህን አትጣል።”
22 እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳቱ፣ በደመናውና በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ለማኅበራችሁ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ የተናገራችሁ ትእዛዞቹ እነዚህ ናቸው፤ የጨመረውም ሌላ የለም፤ ትእዛዞቹንም በሁለት የድንጋይ ጽላት ላይ ጽፎ ሰጠኝ።
23ተራራው በእሳት ሲቃጠል፣ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ፣ እናንተ የየነገዶቻችሁ አለቆችና ሽማግሌዎቻችሁም በሙሉ ወደ እኔ ዘንድ መጣችሁ፤ 24እንዲህም አላችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር ክብሩንና ግርማውን አሳይቶናል፤ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል። እግዚአብሔር አነጋግሮትም እንኳ፣ ሰው በሕይወት ሊኖር እንደሚችል በዛሬው ቀን አይተናል። 25ከእንግዲህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ድምፅ ብንሰማ እንሞታለን፤ ይህችም ታላቅ እሳት ፈጽማ ታጠፋናለች፤ ታዲያ ለምን እንሙት? 26ለመሆኑ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር እኛ እንደ ሰማነው ሁሉ፣ የሕያው እግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቶ በሕይወት ለመኖር የቻለ ከሥጋ ለባሽ ማን አለ? 27አንተ ቅረብ፤ አምላካችን እግዚአብሔር የሚለውን ሁሉ ስሙ፤ ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር የሚነግርህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንሰማለን፤ እናደርገዋለንም።”
28ይህን ስትነግሩኝ እግዚአብሔር ሰማ፤ እግዚአብሔርም አለኝ፤ “ይህ ሕዝብ ምን እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ ያሉትም ሁሉ መልካም ነው። 29ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁልጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!
30“ሄደህ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ ንገራቸው። 31አንተ ግን እንዲወርሷት በምሰጣቸው ምድር እንዲጠብቋቸው የምታስተምራቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ሕጎች ሁሉ እንድሰጥህ እዚሁ ከእኔ ዘንድ ቈይ።”
32እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ለመፈጸም ተጠንቀቁ፤ ቀኝም ግራም አትበሉ። 33በምትወርሷት ምድር በሕይወት ለመኖር እንድትችሉ፣ መልካም እንዲሆንላችሁና ዕድሜያችሁም እንዲረዝም፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።
Currently Selected:
ዘዳግም 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.