ዘዳግም 11
11
እግዚአብሔርን ውደድ፤ ታዘዘውም
1እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፤ ግዴታውን፣ ሥርዐቱን፣ ሕጉንና ትእዛዙን ሁልጊዜ ጠብቅ። 2የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ተግሣጽ ይኸውም ግርማውን፣ ብርቱ እጁንና የተዘረጋች ክንዱን ያዩትና የተለማመዱት ልጆቻችሁ ሳይሆኑ እናንተ እንደ ሆናችሁ ዛሬ አስታውሱ፤ 3በግብጽ መካከል፣ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖንና በመላው አገሩ ላይ ያደረጋቸውን ምልክቶችና የሠራቸውን ነገሮች፣ 4በግብጻውያን ሰራዊት፣ በፈረሶቻቸውና በሠረገሎቻቸው ላይ፣ እናንተን ባሳደዷችሁ ጊዜ በቀይ ባሕር#11፥4 ዕብራይስጡ፣ ያም ሳውፍ ይለዋል፤ ይኸውም የደንገል ባሕር ማለት ነው። ውሃ እንዴት እንዳሰጠማቸውና እግዚአብሔር ፈጽሞ እንዴት እንዳጠፋቸው አስታውሱ፤ 5ከምድረ በዳው አንሥቶ እዚህ እስከምትደርሱ ድረስ፣ ለእናንተ ያደረገላችሁን ያዩት ልጆቻችሁ አልነበሩም፤ 6የሮቤል ልጅ የኤልያብ ልጆች የሆኑትን ዳታንና አቤሮንን ከነቤተ ሰቦቻቸው፣ ከነድንኳናቸውና ከነእንስሳታቸው በመላው እስራኤል መካከል ምድር እንዴት አፏን ከፍታ እንደ ዋጠቻቸው እነርሱ አላዩም። 7የእናንተ ዐይኖች ግን እግዚአብሔር ያደረጋቸውን ሥራዎች ሁሉ አይተዋል።
8ስለዚህ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ወደምትወርሷት ምድር ለመግባትና ለመያዝ ብርታት እንድታገኙ፣ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤ 9ለአባቶቻቸውና ለዘሮቻቸው እግዚአብሔር ሊሰጣቸው በማለላቸው፣ በዚያች ማርና ወተት በምታፈስሰው ምድር ረዥም ዕድሜ ትኖሩ ዘንድ፣ 10የምትገባባት ምድር እንደ ወጣህባትና ዘርህን ዘርተህባት በእግርህ ውሃ እንዳጠጣሃት የአትክልት ቦታ እንደ ግብጽ ምድር አይደለችም። 11ዮርዳኖስን ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፣ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፣ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት። 12ይህች ምድር አምላክህ እግዚአብሔር የሚንከባከባት፣ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዐይን ምን ጊዜም የማይለያት ናት።
13ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች በታማኝነት ብትጠብቁ፣ ይኸውም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትወድዱና በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁም እርሱን በማገልገል በታማኝነት ብትጠብቁ፣ 14እህልህን፣ ወይንህንና ዘይትህን እንድትሰበስብ የበልጉንና የክረምቱን ዝናብ በምድርህ ላይ በየወቅቱ አዘንባለሁ። 15በሜዳ ላይ ለከብቶችህ ሣር እሰጣለሁ፤ አንተም ትበላለህ፤ ትጠግባለህም።
16ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ተታልላችሁ ሌሎች አማልክትን ታመልካላችሁ፤ ትሰግዳላችሁም። 17ከዚያም የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ይነድዳል፤ እርሱም ዝናብ እንዳይዘንብ፣ ምድሪቱም ፍሬ እንዳትሰጥ ሰማያትን ይዘጋል፤ እናንተም እግዚአብሔር ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ወዲያውኑ ትጠፋላችሁ። 18እነዚህን ቃሎቼን፣ በልባችሁና በአእምሯችሁ አኑሯቸው፤ በእጆቻችሁ ላይ ምልክት አድርጋችሁ እሰሯቸው፣ በግንባራችሁም ላይ ይሁኑ። 19ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር። 20በቤትህ መቃኖችና በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው፤ 21ይህን ካደረጋችሁ፣ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ ለመስጠት በማለላቸው ምድር የእናንተና የልጆቻችሁ ዘመን ከምድር በላይ ያሉ ሰማያትን ርቀት ያህል ይሆናል።
22አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፣ በመንገዶቹም ሁሉ ትሄዱና ከርሱም ጋራ ትጣበቁ ዘንድ እንድትከተሏቸው የምሰጣችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቁ፣ 23እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያስወጣቸዋል፤ እናንተም፣ ከእናንተ ይልቅ ታላላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ታስለቅቃላችሁ። 24በእግራችሁ የምትረግጡት ስፍራ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፣ ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ በስተምዕራብ እስካለው ባሕር#11፥24 የሜዲትራንያን ባሕር ነው። ይደርሳል። 25ማንም ሰው ሊቋቋማችሁ አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ማስደንገጣችሁንና መፈራታችሁን በምትሄዱበት በየትኛውም ምድር ሁሉ ላይ ያሳድራል።
26እነሆ፤ ዛሬ በረከትንና መርገምን በፊታችሁ አኖራለሁ፤ 27በረከቱ ዛሬ የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ስትፈጽሙ ሲሆን፣ 28መርገሙ ደግሞ፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የማትፈጽሙ፣ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ለመከተል እኔ ከማዝዛችሁ መንገድ የምትወጡ ከሆነ ነው። 29ልትወርሳት ወደምትሄድባት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር በሚያስገባህ ጊዜ በረከቱን በገሪዛን ተራራ፣ መርገሙን ደግሞ በጌባል ተራራ ላይ ታሰማለህ። 30እነዚህ ተራሮች የሚገኙት ከዮርዳኖስ ማዶ#11፥30 ወይም፣ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ። ፀሓይ በምትጠልቅበት አቅጣጫ ካለው መንገድ በስተምዕራብ በዓረባ በሚኖሩ የከነዓናውያን ምድር ውስጥ ከጌልገላ ፊት ለፊት፣ በሞሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ አይደለምን? 31አምላካችሁ እግዚአብሔር በሚሰጣችሁ ምድር ትገቡባትና ትወርሷት ዘንድ ዮርዳኖስን ልትሻገሩ ስለ ሆነ፣ ምድሪቱን ወርሳችሁ በምትኖሩባት ጊዜ፣ 32ዛሬ በፊታችሁ እኔ ያስቀመጥኋቸውን ሥርዐቶችና ሕጎች ሁሉ ለመፈጸም ተጠንቀቁ።
Currently Selected:
ዘዳግም 11: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.