ዘዳግም 12
12
ብቸኛው የማምለኪያ ስፍራ
1የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር፣ እንድትወርሷት በሰጣችሁ ምድር ላይ በምትኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ በጥንቃቄ ልትከተሏቸው የሚገባችሁ ሥርዐቶችና ሕግጋት እነዚህ ናቸው። 2ከምድራቸው የምታስለቅቋቸው አሕዛብ በረዣዥም ተራሮች፣ በኰረብቶችና በእያንዳንዱ ዛፍ ሥር አማልክታቸውን የሚያመልኩባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ። 3መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቈራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ።
4በእነርሱ መንገድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አታምልኩ። 5ዳሩ ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፣ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ እሹ፤ ወደዚያም ስፍራ ሂዱ። 6ወደዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ ስእለቶቻችሁንና የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን፣ የቀንድ ከብት መንጋችሁን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አምጡ። 7በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ትበላላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እናንተን በባረከበት፣ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተ ሰዎችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ።
8ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፣ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤ 9ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም። 10ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና አምላካችሁ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፣ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል። 11ከዚያም አምላካችሁ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ። 12እዚያም እናንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፣ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ሐሤት አድርጉ። 13የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በፈለግኸው ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። 14ከነገዶችህ መካከል በአንዱ፣ እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ ብቻ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችህን አቅርብ፤ እዚያም እኔ የማዝዝህን ሁሉ ጠብቅ።
15ሆኖም ከአምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በረከት፣ በየትኛውም ከተማህ፣ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኵላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል። 16ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 17የእህልህን፣ የወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት ወይም የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት፣ ወይም ለመስጠት የተሳልኸውን ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታህን፣ ወይም የእጅህን ስጦታ፣ በከተሞችህ ውስጥ መብላት የለብህም። 18አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ የሚኖር ሌዋዊም፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበሉታላችሁ፤ እጅህም በነካው ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይልሃል። 19በምድርም ላይ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትለው ተጠንቀቅ።
20አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህ፣ ሥጋ አምሮህ፣ “ሥጋ መብላት እፈልጋለሁ” በምትልበት ጊዜ፣ ያሠኘህን ያህል ሥጋ መብላት ትችላለህ። 21ስሙን ለማኖር አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ የራቀ ከሆነ፣ ባዘዝሁህ መሠረት ከቀንድ ከብትህ፣ ከበግና ከፍየል መንጋህ እንስሳት ማረድ ትችላለህ፤ በከተሞችህ ውስጥ የምትፈልገውን ያህል መብላት ትችላለህ፤ 22ሚዳቋ ወይም ድኵላ እንደሚበላ አድርገህ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆኑትና ያልሆኑት ሊበሉ ይችላሉ። 23ደሙን ግን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደም ሕይወት ስለ ሆነ፣ ሥጋን ከነሕይወቱ አትብላ። 24ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 25በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ መልካም እንዲሆንላቸው አትብላው።
26ነገር ግን የተቀደሱ ነገሮችህን ለመስጠት የተሳልሃቸውን ሁሉ ይዘህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ። 27የሚቃጠል መሥዋዕትህን፣ ሥጋውንም ደሙንም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ። የመሥዋዕትህ ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን መብላት ትችላለህ። 28በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ ለዘላለም መልካም እንዲሆንላችሁ፣ እኔ የምሰጥህን እነዚህን ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ፈጽማቸው።
29የምትወርሯቸውንና የምታስለቅቋቸውን አሕዛብ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ባስወጣችኋቸውና በምድራቸው በተቀመጣችሁ ጊዜ ግን፣ 30ከፊትህ ከጠፉ በኋላ፣ “እነዚህ ሕዝቦች አማልክታቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ” ብለህ በመጠየቅ እንዳትጠመድ ተጠንቀቅ። 31አምላክህን እግዚአብሔርን በእነርሱ መንገድ ፈጽሞ አታምልክ፤ ምክንያቱም አማልክታቸውን ሲያመልኩ እግዚአብሔር የሚጸየፈውን ሁሉንም ዐይነት ነገር ያደርጋሉና፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን እንኳ ለአማልክታቸው መሥዋዕት አድርገው ያቃጥላሉ።
32እኔ ያዘዝሁህን ሁሉ ጠብቅ፤ አትጨምርበት፤ አትቀንስለትም።
Currently Selected:
ዘዳግም 12: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.