የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘዳግም 32

32
1ሰማያት ሆይ፤ አድምጡ፤ እኔም እናገራለሁ፤
ምድር ሆይ፤ አንቺም የአፌን ቃል ስሚ።
2ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትውረድ፤
ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠብ፤
በቡቃያ ሣር ላይ እንደ ካፊያ፣
ለጋ ተክልም ላይ እንደ ከባድ ዝናብ ይውረድ።
3እኔ የእግዚአብሔርን ስም ዐውጃለሁ፤
የአምላካችንን ታላቅነት አወድሱ!
4እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤
መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤
የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣
ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው።
5በርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም፤
ወልጋዳና ጠማማ ትውልዶች ናቸው#32፥5 ወይም የተጣመሙት እነርሱ እንጂ የርሱ ልጆች አይደሉም።
6አንተ ሞኝና ጥበብ የጐደለህ ሕዝብ፣
እግዚአብሔር የምትመልስለት በዚህ መንገድ ነውን?
አባትህ ፈጣሪህ#32፥6 ወይም ያወጣህ አባትህ።
የሠራህና ያበጀህ እርሱ አይደለምን?
7የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤
አባትህን ጠይቅ፤ ይነግርሃልም፤
ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ያስረዱሃል።
8ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን በሰጠ ጊዜ፣
የሰውንም ዘር በለያየ ጊዜ፣
በእስራኤል ልጆች#32፥8 የማሶሬቱ ቅጅ፣ የሙት ባሕር ጥቅልል እንዲሁም የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይላሉ። ቍጥር ልክ፣
የአሕዛብን ርስት ድንበር ለየ፤
9እግዚአብሔር ድርሻ የገዛ ሕዝቡ፣
ያዕቆብ የተለየ ርስቱ ነውና።
10እርሱን በምድረ በዳ፣
ባዶና ጭው ባለ በረሓ ውስጥ አገኘው፤
ጋሻ ሆነው፤ ተጠነቀቀለትም፤
እንደ ዐይኑ ብሌን ጠበቀው።
11ንስር ጐጆዋን በትና፣
በጫጩቶቿም ላይ እንደምትረብብ፣
እነርሱን ለመያዝ ክንፎቿን እንደምትዘረጋ፣
በክንፎቿም እንደምትሸከማቸው፣
12 እግዚአብሔር ብቻ መራው፤
ምንም ባዕድ አምላክ ዐብሮት አልነበረም።
13በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤
የዕርሻንም ፍሬ መገበው።
ከዐለት ድንጋይ ማር አበላው፤
ከባልጩትም ድንጋይ ዘይት መገበው።
14የላሙንና የበጉን መንጋ ቅቤና ወተት፣
የሰቡትን በጎችና ፍየሎች፣
የባሳንን ምርጥ አውራ በግ፣
መልካም የሆነውንም ስንዴ፣
ማለፊያውንም የወይን ጠጅ።
15ይሹሩን#32፥15 ይሹሩን ማለት ቅን ወይም ትክክለኛ ማለት ሲሆን፣ ይኸውም እስራኤልን የሚያሳይ ነው። ወፈረ፤ ረገጠ፤
ጠገበ፤ ሰውነቱ ደነደነ፤ ለሰለሰ፤
የፈጠረውንም አምላክ ተወ፤
መጠጊያ ዐለት የሆነውን አዳኙንም ናቀ።
16በባዕዳን አማልክታቸው አስቀኑት፤
በአስጸያፊ ጣዖቶቻቸውም አስቈጡት።
17አምላክ ላልሆኑ አጋንንት፦
ላላወቋቸው አማልክት፣
ከጊዜ በኋላ ለተነሡ አማልክት፣
አባቶቻችሁ ላልፈሯቸው አማልክት ሠዉ።
18አባት የሆነህን ዐለት ከዳኸው፤
የወለደህን አምላክ ረሳኸው።
19 እግዚአብሔር ይህን አይቶ ናቃቸው፤
በወንድና በሴት ልጆቹ ተቈጥቷልና።
20እርሱም፣ “ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤
መጨረሻቸው ምን እንደሚሆንም አያለሁ” አለ፤
ጠማማ ትውልድ፣
የማይታመኑም ልጆች ናቸውና።
21አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤
በከንቱ ጣዖቶቻቸው አስቈጡኝ።
እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤
በሞኝ ሕዝብም አስቈጣቸዋለሁ።
22በቍጣዬ እሳት ተቀጣጥሏልና፤
እርሱ እስከ ሲኦል ዘልቆ ይነድዳል።
ምድርን እስከ ሰብሏ ይበላል፤
የተራሮችንም መሠረት ያቀጣጥላል።
23“በመዓት ላይ መዓት አመጣባቸዋለሁ።
ፍላጻዬንም በእነርሱ ላይ እጨርሳለሁ።
24የሚያጠፋ ራብ፣ በልቶ የሚጨርስ ቸነፈርና ከባድ
መቅሠፍት እሰድድባቸዋለሁ፤
የአራዊትን ሹል ጥርስ፣ በምድር የሚሳብ የእባብ መርዝም
እሰድድባቸዋለሁ።
25ሰይፍ መንገድ ላይ ያስቀራቸዋል፤
ቤታቸውም ውስጥ ድንጋጤ ይነግሣል፤
ጕልማሳውና ልጃገረዷ፣
ሕፃኑና ሽማግሌው ይጠፋሉ።
26እበትናቸዋለሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን
አጠፋለሁ አልሁ፤
27ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ፣
‘ድል ያደረገችው እጃችን እንጂ፣
እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አላደረገም’ እንዳይሉ፣ 
የጠላትን መነሣሣት ሠጋሁ።”
28አእምሮ የጐደላቸው፣
ማስተዋልም የሌላቸው ሕዝብ ናቸው።
29አስተዋዮች ቢሆኑ ኖሮ ይህን በተገነዘቡ፣
መጨረሻቸውም ምን እንደሚሆን ባስተዋሉ ነበር።
30መጠጊያ ዐለታቸው ካልሸጣቸው፣
እግዚአብሔር ካልተዋቸው በቀር፣
አንድ ሰው እንዴት ሺሑን ያሳድዳል?
ሁለቱስ እንዴት ዐሥር ሺሑን እንዲሸሹ ያደርጋሉ?
31የእነርሱ መጠጊያ ዐለት እንደ እኛ መጠጊያ
ዐለት አይደለምና፤ ጠላቶቻችንም እንኳ ይህን አይክዱም።
32ወይናቸው ከሰዶም ወይን፣
ከገሞራም ዕርሻ ይመጣል፤
የወይናቸው ፍሬ በመርዝ፣
ዘለላቸውም በምሬት የተሞላ ነው።
33ወይናቸው የእባብ መርዝ፣
የመራዥ እባብም መርዝ ነው።
34“ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ ያለ፣
በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን?
35በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፤
ጊዜው ሲደርስ እግራቸው ይሰናከላል፤
የመጥፊያቸው ቀን ቀርቧል፤
የሚመጣባቸውም ፍርድ ፈጥኖባቸዋል።”
36ኀይላቸው መድከሙን፣
ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አለመቅረቱን በሚያይበት ጊዜ፣
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፤
ለአገልጋዮቹም ይራራል።
37እንዲህም ይላል፤ “መጠጊያ ዐለት የሆኗቸው፣
እነዚያ አማልክታቸው የት አሉ?
38የመሥዋዕታቸውን ሥብ የበሉ፣
የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ አማልክት ወዴት ናቸው?
እስኪ ይነሡና ይርዷችሁ!
እስኪ መጠለያ ይስጧችሁ!
39“እኔ ራሴ እርሱ እንደ ሆንሁ እዩ፤
ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤
እገድላለሁ፤ አድናለሁም፤
አቈስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤
ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም።
40እጄን ወደ ሰማይ አነሣለሁ፤
ለዘላለምም ሕያው እንደ ሆንሁ እናገራለሁ፤
41የሚያብረቀርቅ ሰይፌን ስዬ፣
እጄ ለፍርድ ስትይዘው፣
ባላጋራዎቼን እበቀላቸዋለሁ፤
የሚጠሉኝንም እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ።
42ሰይፌ ሥጋ በሚበላበት ጊዜ፣
ፍላጾቼ በደም እንዲሰክሩ አደርጋለሁ፤
ደሙ የታረዱትና የምርኮኞች፣
የጠላት አለቆችም ራስ ደም ነው።”
43አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋራ ደስ ይበላችሁ#32፥43 ወይም፣ ሕዝቦች ሆይ፤ ደስ ይበላችሁ።#32፥43 የማሶሬቱ ቅጅ፣ የሙት ባሕር ጥቅልል እንዲሁም የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም፣ ሕዝቦች ሆይ፤ መላእክት ሁሉ ለርሱ ይስገዱ ይላሉ።
እርሱ የአገልጋዮቹን ደም ይመልሳል፤
ጠላቶቹንም ይበቀላል።
ምድሪቱንና ሕዝቡን ያነጻልና።
44ሙሴም ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ጋራ መጥቶ የዚህን መዝሙር ቃሎች በሕዝቡ ጆሮ ተናገረ። 45ሙሴም እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለመላው እስራኤል ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ 46እንዲህ አላቸው፤ “የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዟቸው፣ እኔ ዛሬ በግልጽ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ። 47ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃሎች አይደሉም፤ በእነርሱ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ በምትወርሷትም ምድር ረዥም ዘመን ትኖራላችሁ።”
ሙሴ በናባው ተራራ ላይ መሞቱ
48በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 49“ከኢያሪኮ ማዶ ባለው የሞዓብ ምድር፣ ከዓባሪም ተራሮች አንዱ ወደ ሆነው ወደ ናባው ተራራ ወጥተህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርጌ የምሰጣትን የከነዓንን ምድር አሻግረህ ተመልከት። 50ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ ላይ እንደ ሞተና ወደ ወገኖቹ እንደ ተሰበሰበ ሁሉ፣ አንተም በወጣህበት በዚያ ተራራ ላይ ሙት፤ ወደ ወገኖችህም ተሰብሰብ። 51ይህ የሚሆንበት ምክንያት ሁለታችሁም በጺን ምድረ በዳ፣ በቃዴስ መሪባ ውሃ አጠገብ በእኔ ላይ መታመናችሁን በእስራኤላውያን ፊት ስላጐደላችሁና ቅድስናዬንም በእስራኤላውያን መካከል ስላላከበራችሁ ነው። 52ስለዚህ ምድሪቱን ከሩቅ ሆነህ ታያታለህ እንጂ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ወደምሰጣት ምድር አትገባም።”

Currently Selected:

ዘዳግም 32: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ