ዘዳግም 33

33
ሙሴ የእስራኤልን ነገዶች ባረከ
33፥1-29 ተጓ ምብ – ዘፍ 49፥1-28
1እግዚአብሔር ሰው ሙሴ ከመሞቱ በፊት ለእስራኤላውያን የሰጠው ቃለ ቡራኬ ይህ ነው፤ 2እንዲህም አለ፦
እግዚአብሔር ከሲና መጣ፤
በእነርሱም ላይ ከሴይር እንደ ማለዳ ፀሓይ ወጣ፤
ከፋራን ተራራ አበራላቸው፤
ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋራ#33፥2 ወይም በአእላፋት ቅዱሳኑ። መጣ፤
በስተ ቀኙ የሚነድድ እሳት ነበር።
3በርግጥ ሕዝቡን የምትወድድ አንተ ነህ፤
ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ውስጥ ናቸው።
ከእግርህ ሥር ሁሉ ይሰግዳሉ፤
ከአንተ ትእዛዝ ይቀበላሉ፤
4ይህ ሙሴ የሰጠን ሕግ፣
የያዕቆብ ጉባኤ ርስት ነው።
5የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ጋራ ሆነው፣
በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ፣
እርሱ በይሹሩን#33፥5 በዚህ ስፍራና በቍጥር 26 ላይ ይሽሩን ማለት፣ ቅን ወይም ትክክለኛ ማለት ሲሆን ይኸውም እስራኤልን የሚያሳይ ነው። ላይ ንጉሥ ነበር።
6“ሮቤል በሕይወት ይኑር፤ አይሙት፤
የወገኖቹ ቍጥርም አይጕደልበት።”
7ስለ ይሁዳ የተናገረው ይህ ነው፦
እግዚአብሔር ሆይ፤ የይሁዳን ጩኸት ስማ፤
ወደ ወገኖቹም አምጣው።
በገዛ እጆቹ ራሱን ይከላከላል፤
አቤቱ ከጠላቶቹ ጋራ ሲዋጋ ረዳቱ ሁን!”
8ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፦
“ቱሚምህና ኡሪምህ፣
ለምታምነው ሰው ይሁን፤
ማሳህ በተባለው ቦታ ፈተንኸው፤
በመሪባም ውሃ ከርሱ ጋራ ተከራከርህ።
9ስለ አባቱና ስለ እናቱ ሲናገርም፣
‘ስለ እነርሱ ግድ የለኝም’ አለ።
ወንድሞቹን አልለያቸውም፤
ልጆቹንም አላወቃቸውም።
ለቃልህ ግን ጥንቃቄ አደረገ፤
ኪዳንህንም ጠበቀ።
10ሥርዐትህን ለያዕቆብ፣
ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራል።
ዕጣን በፊትህ፣
የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ በመሠዊያህ ላይ ያቀርባል።
11 እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀይሉን ሁሉ ባርክለት፤
በእጁ ሥራ ደስ ይበልህ፤
በርሱ ላይ የሚነሡበትን ሽንጣቸውን ቍረጠው፤
ጠላቶቹንም እንዳያንሠራሩ አድርገህ ምታቸው።”
12ስለ ብንያም እንዲህ አለ፦
“የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ በርሱ ተጠብቆ ያለ ሥጋት ይረፍ፤
ቀኑን ሙሉ ይጋርደዋልና፤
እግዚአብሔር የሚወድደውም ሰው በትከሻዎቹ መካከል ያርፋል።”
13ስለ ዮሴፍ ደግሞ እንዲህ አለው፦
እግዚአብሔር ምድሩን ይባርክ፤
ድንቅ የሆነውን ጠል ከላይ ከሰማይ በማውረድ፣
ከታች የተንጣለለውን ጥልቅ ውሃ
14ፀሓይ በምታስገኘው ምርጥ ፍሬ፣
ጨረቃም በምትሰጠው እጅግ መልካም ምርት፤
15ከጥንት ተራሮች በተገኘ ምርጥ ስጦታ፣
በዘላለማዊ ኰረብቶች ፍሬያማነት፤
16ምድር በምታስገኘው ምርጥ ስጦታና በሙላቷ፣
በሚቃጠለው ቍጥቋጦም ውስጥ በነበረው በርሱ ሞገስ።
እነዚህ ሁሉ በወንድሞቹ መካከል ገዥ በሆነው፣
በዮሴፍ ዐናት ላይ ይውረዱ።
17በግርማው እንደ በኵር ኰርማ ነው፤
ቀንዶቹም የጐሽ ቀንዶች ናቸው።
በእነርሱም ሕዝቦችን፣
በምድር ዳርቻ ላይ ያሉትን እንኳ ሳይቀር ይወጋል፤
እነርሱም የኤፍሬም ዐሥር ሺሕዎቹ ናቸው፤
የምናሴም ሺሕዎቹ እንደዚሁ ናቸው።”
18ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ፦
“ዛብሎን ሆይ፤ ወደ ውጭ በመውጣትህ፣
አንተም ይሳኮር በድንኳኖችህ ውስጥ ደስ ይበልህ፤
19አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፤
በዚያም የጽድቅን መሥዋዕት ያቀርባሉ።
በባሕሮች ውስጥ ያለውን በተትረፈረፈ ብልጽግና፣
በአሸዋውም ውስጥ የተደበቀውን ሀብት ይደሰቱበታል።”
20ስለ ጋድም እንዲህ አለ፦
“የጋድን ግዛት የሚያሰፋ የተመሰገነ ነው!
ክንድንና ራስን በመገነጣጠል፣
ጋድ እንደ አንበሳ በዚያ ይኖራል።
21ለም የሆነውን መሬት ለራሱ መረጠ፤
የአለቃም ድርሻ ለርሱ ተጠብቆለታል።
የሕዝቡ መሪዎች በተሰበሰቡ ጊዜ፣
እግዚአብሔርን የጽድቅ ፈቃድና፣
በእስራኤል ላይ የበየነውን ፍርዱን ፈጸመ።”
22ስለ ዳንም እንዲህ አለ፦
“ዳን ከባሳን ዘልሎ የሚወጣ፣
የአንበሳ ደቦል ነው።”
23ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ፦
“ንፍታሌም በእግዚአብሔር ሞገስ ረክቷል፤
በበረከቱም ተሞልቷል፤
ባሕሩንና የደቡብን ምድር ይወርሳል።”
24ስለ አሴርም እንዲህ አለ፦
“አሴር ከሌሎች ልጆች ይልቅ የተባረከ ነው፤
በወንድሞቹ ዘንድ ተወዳጅ ይሁን፤
እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ።
25የደጃፍህ መቀርቀሪያ ብረትና ናስ ይሆናል፤
ኀይልህም በዘመንህ ሁሉ ይኖራል።
26“አንተን ለመርዳት በሰማያት ላይ፣
በደመናትም ላይ በግርማው እንደሚገሠግሥ፣
እንደ ይሹሩን አምላክ ያለ ማንም የለም።
27ዘላለማዊ አምላክ መኖሪያህ ነው፤
የዘላለም ክንዶቹም ከሥርህ ናቸው፤
‘እርሱን አጥፋው!’ በማለት፣
ጠላትህን ከፊትህ ያስወግደዋል።
28ስለዚህ እስራኤል ብቻውን ያለ ሥጋት ይኖራል፤
የሰማያት ጠል በሚወርድበት፣
እህልና የወይን ጠጅ ባለበት ምድር፣
የያዕቆብን ምንጭ የሚነካው የለም።
29ብፁዕ ነህ፤
አንተ እስራኤል ሆይ፤
እግዚአብሔር ያዳነው ሕዝብ፣
እንደ አንተ ያለ ማን አለ?
እርሱ ጋሻህና ረዳትህ፣ የክብርህም ሰይፍ ነው።
ጠላቶችህ በፍርሀት ከፊትህ ያፈገፍጋሉ፤
አንተም የማምለኪያ ኰረብታቸውን
መረማመጃ ታደርጋለህ።”

Currently Selected:

ዘዳግም 33: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ