የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘዳግም 8

8
እግዚአብሔርን አትርሳ
1በሕይወት እንድትኖሩ፣ እንድትበዙና እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በመሐላ ተስፋ የገባላቸውን ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፣ ዛሬ እኔ የምሰጥህን እያንዳንዱን ትእዛዝ ለመከተል ጥንቃቄ አድርጉ። 2አምላክህ እግዚአብሔር ትእዛዞቹን መጠበቅህንና በልብህ ያለውን ለማወቅ፣ ትሑት ሊያደርግህና ሊፈትንህ በእነዚህ አርባ ዓመታት በዚህ ምድረ በዳ ጕዞህ ሁሉ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ። 3ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው በእያንዳንዱ ቃል እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ሊያስተምርህ አስራበህ፤ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቁትን መና መገበህ፤ 4በእነዚህ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብስህ አላለቀም፤ እግርህም አላበጠም። 5ስለዚህ ሰው ልጁን እንደሚቀጣ፣ አምላክህ እግዚአብሔርም አንተን እንደሚቀጣህ በልብህ ዕወቅ።
6በመንገዶቹ በመሄድና እርሱንም በማክበር፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ጠብቅ። 7አምላክህ እግዚአብሔር ጅረቶችና የኵሬ ውሃ ወዳለበት፣ ምንጮች ከየሸለቆውና ከየኰረብታው ወደሚፈስሱበት ወደ መልካሚቱ ምድር ያገባሃል፣ 8ስንዴና ገብስ፣ ወይንና የበለስ ዛፎች፣ ሮማን፣ የወይራ ዘይትና ማር የሚገኝባት ምድር፤ 9ምንም ነገር የማይታጣባት፣ የዳቦም ዕጦት የሌለባት፣ ዐለቶች ብረት የሆኑባት፣ ከኰረብቶቿም መዳብ ቈፍረህ ልታወጣ የምትችልባት ምድር ናት።
10በልተህ በምትጠግብበት ጊዜ እንዲህ ያለች መልካም ምድር ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን ባርከው። 11በዛሬዪቱ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሕጉንና ሥርዐቱን ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳው ተጠንቀቅ። 12አለዚያ በልተህ ስትጠግብና ጥሩ ጥሩ ቤቶችን ሠርተህ መኖር ስትጀምር፣ 13ደግሞም የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህ ሲበዛ፣ ብርህና ወርቅህ ሲበረክት፣ ያለህም ሁሉ በላይ በላዩ እየጨመረ ሲሄድ፣ 14ልብህ ይታበይና ከባርነት ምድር፣ ከግብጽ ያወጣህን አምላክህን እግዚአብሔርን ትረሳለህ። 15በዚያ ጭልጥ ባለና አስፈሪ ምድረ በዳ፣ በዚያ በሚያስጠማና ውሃ በማይገኝበት ደረቅ መሬት፣ መርዘኛ እባብና ጊንጥ ባለበት ምድረ በዳ መራህ፤ ከጽኑ ዐለትም ውሃ አፈለቀልህ። 16በመጨረሻ መልካም እንዲሆንልህ፣ አንተን ትሑት ለማድረግና ለመፈተን፣ አባቶችህ ፈጽሞ የማያውቁትን መና በምድረ በዳ መገበህ። 17ምናልባትም፣ “ይህን ሀብት ያፈራሁት በጕልበቴና በእጄ ብርታት ነው” ብለህ በልብህ ታስብ ይሆናል። 18ነገር ግን ሀብት እንድታፈራ ችሎታ የሰጠህ፣ ለአባቶችህም በመሐላ የገባውን ኪዳን ያጸናልህ እርሱ ስለ ሆነ፣ አምላክህን እግዚአብሔርን ዐስበው።
19አምላክህን እግዚአብሔርን ብትረሳና ሌሎችን አማልክት ብትከተል፣ ብታመልክና ለእነርሱ ብትሰግድላቸው በርግጥ እንደምትጠፉ ዛሬ እመሰክርባችኋለሁ። 20እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያሉትን አሕዛብ እንዳጠፋቸው ሁሉ፣ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛችሁ እናንተም ትጠፋላችሁ።

Currently Selected:

ዘዳግም 8: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ